Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ በምትረከበውን የባህር በር ስፍራ ላይ የሁለቱም አገራት ባለስልጣናት መከሩ

“ኢትዮጵያ በክልላዊ ጫና ዉስጥ በመሆኗ የሶማሌላንድን እዉቅና ልትሰርዝ ትችላለች ተባለ” ሲል ኢትዮኤፍ ኤም ብሉምበርግን ጠቅሶ የዘገበው ዜና ፍጹም መሰረት ቢስ መሆኑ ተረጋገጠ።

በስምምነቱ የተነሳ የተፈጠረዉን ቀጣናዊ ዉጥረት ለማርገብ አለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ ባለበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ መንግስት እውቅና ለመስጠት የያዘችዉን እቅድ ለመሰረዝ እያሰበች ነዉ መባሉን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ነግረዉኛል ሲል ብሉምበርግ መዘገቡ ነው በዜናው የተጠቀሰው። ማንነቱ በህልውናው ጦርነት ወቅት በወጉ የሚታወቀው የብሉምበርጉ ዘጋቢ ዜና “ኢትዮጵያዊያ ነን” በሚሉ ሚዲያዎች ሳይቀር እንደወረደ ሲሰራጭ ዜናውን ከመንግስት አካል ለማረጋገጥ እንኳን አልተወደደም።

የሉዓላዊ ሚዲያ አዘጋጅና ባለቤት ሲሳይ አጌና ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት መስማቱን ጠቅሶ ዜናው የተሳሳተ መሆኑን ዘግቧል። ከሁሉም በላይ ግን ከሶማሊ ላንድ የሚወጡ ዜናዎች ዜናውን አክሽፈውታል። በቪዲዮ ተደግፎ በተሰራጨው የሶማሊ ላንድ ዜና የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የመከላከያ ከፍተኛ ሹሞች ከሶማሊላንድ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን ኢትዮጵያ በሊዝ ትረከበዋለች በተባለው የባህር በር ስፍራ ላይ ሆነው የመስክ ምልከታ ሲያደርጉ አሳይተዋል።

ብሉምበርግም ሆነ የብሉምበርግን ዜና ያራቡ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች፣ ዜናውን ባሰራጩበት ቅጽበት ይህ መረጃ ሲሰራጭ ቢያንስ ለማመጣጠን ሲሞክሩ ወይም እንደ ዜና አልዘገቡትም።

ኢትዮ12 ያነገራቸውና ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የመንግስት ሃላፊዎች እንዳሉት ” የተቀየረ አቋምም ሆነ ድርድር የለም። ነገር ግን ከሶማሌ ጋር ሰላም ስለምንሻ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ ነው። ጩኸትና ልፍለፋ ያልተፈለገው ለዚህ ነው። ሁሉም ጉዳይ ስልት ተላብሶ ቀጥሏል። መጨረሻውም ተቃርቧል። የሶማሊላንድ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የባህር በር ዜናም አለ” ብለዋል።

“የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ ጥር ወር ከሶማሌላንድ ጋር የመጀመሪያ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፤ይህም ከፊል ራስ ገዝ ለሆነችዉ የሶማሊያ ክልል ሉዓላዊነት እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር እንድትሆን በምላሹም ለ50 አመታት የኤደን ባህረ ሰላጤን እንድትጠቀም የሚያደርግ ነበር ” ያለው ብሉምበርግ፣ “ስምምነቱ በጎረቤት ሀገራት ግርግርን የፈጠረ ፤ሶማሊያ የግዛት አንድነቴን እጠብቃለሁ ስትል የተቆጣችበት፣ ግብፅ እና ሌሎች ሀገራትም ማስጠንቀቂያ የሰጡበት ጉዳይ ነው” የሚል ማስታወሻም አስፍሯል።

“የቅርብ ሰዎች ነገሩኝ” ሲል ለዘገበው ዘገባ መነሻ ያደረገው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ባለፈው ሳምንት በናይሮቢ በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸው መገለጹን ተከትሎ ነው።

በደማቅ አቀባበል ናይሮቢ የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፣ “ወንድም” ሲሉ ከሚጠሯት ሶማሊያ ጋር ምንም ዓይነት ጸብ እንዲፈጠር እንደማይፈልጉ፣ ይህ የመንግስታቸው አቋም የጸና እንደሆነ በተደጋጋሚ በአደባባይ ማመልክታቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ብሉምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት ናይሮቢ ላይ ብቻ እንደሆነ በማስመሰል፣ ይህም የሆነው በጫና እንደሆነ በመግለጽ ” ውስጥ አዋቂዎች ነገሩኝ” ሲል ዜናውን ታማኝ ለማድረግ ሞክሯል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሶማሊያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በስምምነቱ ዉስጥ ካሉ በጣም አወዛጋቢ ጉዳዮች ለመውጣት ፈቃደኛ መሆናቸውን ስለመግለጻቸዉ ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ ስልጣን የለንም ያሉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰዎች ነግረዉኛል ብሏል” ሲል ብሉምበርግ ዜናውን እውነታ ለማላበስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የናይሮቢ ውይይትና ጉብኘት ተንተርሷል። ይሁን እንጂ የሶማሊላንድ መገናኛዎች ምንጭ ጠቅሰው ሳይሆን በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ በማቅርብ ስምምነቱ ወደ ተግባር እየተቃረበ መሆኑን አመላክተዋል።

” መንግስት ለምን ማስተባበያ አልሰጠም” በሚል የተጠየቁት ሃላፊዎች ” መንግስት እንዲህ ያለ የሚዲያ አተካራ ውስጥ አይገባም። አገር ወዳድ የሆኑና የአገራቸው ጥቅም የሚበልጥባቸው ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ላይ ያለው አቋምና ማንነቱ በግልጽ የሚታወቀውን የብሉምበርግ ጸሃፊ ቢያንስ ምንጭ ከማድረግ ሊቆጠቡ ይገባል። ለሁሉም ግን ብሄራዊ ጥቅማቸውን የሚያሰሉ የስማሊላንድ አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች እንዲሁም ዜጎች የሰጡት ምላሽ በቂ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ብሉምበርግ “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሀገሪቱ ለሶማሌላንድ ያላትን እውቅና ለማቋረጥ ፍቃደኛ ልትሆን እንደምትችል ለውጭ ባለስልጣናት በግል ነግረዋቸዋል” በሚል ይዝሰራጨው ዜና ፍጹም ሃሰት መሆኑን ያመለከቱት ወገኖች፣ ” ዜናው “የአዲስ አበባን አቋም በተመለከተ የተነገራቸው አምስት የውጭ ባለስልጣናት ናቸው” ሲል መዘገቡ ዜናውን እውነት ለማስመሰል መጋጋጡን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል። አያይዘውም በጉዳዩ ላይ እንኳን ከናይሮቢ፣ ሩቅ ካሉ አገራትም ጋር ንግግር ስለመኖሩ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ በተደጋጋሚ የተናገሩት፣ ወደፊትም የሚናገሩት ጉዳይ ነውና ሚዛን እንደማያነሳ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ናይሮቢ በነበሩበት ተመሳሳይ ጊዜ ኬንያን እየጎበኙ ከሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። በሩቶ አማካይነት በተደረገው ውይይት ስለ ባህር በር ጉዳይ አንስተው እንደሚወያዩ ግልጽ መሆኑን ማንም ባይናገርም የሚታወቅ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ይመስላል የሶማሊያ መንግስት የሚዲያ ጩኸት ቀንሷል።

በእርግጥ ሩቶ በጥር ወር ለብሉምበርግ በሰጡት ቃለ ምልልስ መንግስታቸዉ ኢትዮጵያ ከወደብ ፍላጎት በላይ ሌሎች አማራጮችን እንድታስብ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑን አመልክተው ነበር። አማራጭ ያሉትን ይፋ ባያደርጉም ከጉብኝቱ በሁዋላ የለቡ ወደብ ለኢትዮጵያ አማራጭ መሆኑ በገሃድ የታየበት፣ የመንገድ ግንባታው መገባደዱና አገለግሎቱ እንዳይታወክ የጸጥታ ስራ ለመስራት ሙሉ ስምምነት መደረጉ ይታወሳል።

ከአንድ በላይ የባህር በርና ወደብ እንደሚያሻት ደጋግማ ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ ኬንያ ላይ በለቡ ወደብ ለመጠቀም፣ የኤሌክትሪክ ኤክስፖርቷን እንደምታሳድግ ብታስታውቅም፣ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን አመልክቶ ይህ እስከተጻፈ ድረስ የተቋረጠ ወይም የሚታወቅ የአቋም ለውጥ አልተስማም። እንደውም ውሉን አጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት ከጫፍ ላይ መደረሱ ነው እየተሰማ ያለው።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107 ፣ “ሶማሊያ ህገወጥ ነው ያለችው እና የግዛት መካለልን ይወክላል ያለችውን ይህን ስምምነት ቀድሞውንም ተለዋዋጭ በሆነው ክልል ውስጥ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ጎረቤት ሀገራት እና አንዳንድ የኢትዮጵያ ትልልቅ ለጋሾች ስጋታቸውን ከዚህ በፊት መግለጻቸዉም የሚታወስ ነዉ” ሲል የብሉምበርግን ዜና በራሱ ማስታወሻ አጅቦታል።

“አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስምምነቱ እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ሁኔታውን ለመመልመያው እንዲጠቀምበት ሊፈቅድለት ይችላል ሲሉም ስጋታቸዉን ገልጸዋል” ሲል ስጋታቸውን ስጋቱ አድርጎ ኢትዮ ኤፍ ኤም 107 ዘግቧል።

ኢትዮ12 ባላት መረጃ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላት ስምምነት ፈርጀ ብዙ እንደሆነና ዋና ዋና በሚባሉ የዓለም አገራት ድጋፍ ያለው ነው። በቅርቡ እንግሊዝ ከኢትዮጵያና ከኬንያ ጋር ያደረገችው የቀይባህርን ሰላም የማስጠበቅ ስምምነት የዚሁ ማሳይ እንደሆነ ተደርጎ በበርካቶች ዘንዳ እየተገለጸ ነው። የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዝግጁነትም ተደጋግሞ እየተገለጸ ያለው ለዚሁ ነው።

ኢትዮጵያ የተጠቀሰውን የኤደን ባህረ ሰላጤ አካል የሆነውን ቁልፍ የባህር በር ከወሰደች በቀይ ባህር መውጫና መግቢያ ላንቃ ላይ የምትገነባው የጦር ሃይል ቀይ ባህር ላይ ካሉት ግብጽና ኤርትራ በላይ በፖለቲካ ጡንቻ የሚሰጣት እንደሆነ ባለሙያዎች መስክረዋል። የግብጽና ኤርትራ ጩኸትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አመልክተዋል። እስራኤል በይፋ ኢትዮጵያን እንደምትደግፍ መገለጹም አይዘነጋም።

Exit mobile version