Site icon ETHIO12.COM

ጓቲማላ ወደ አሜሪካ ሊያቀኑ ያሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አገደች

 

ወደ አሜሪካ የሚጓዙ የመካከለኛው አሜሪካ ስደተኞች ቡድን በጓቲማላ የፀጥታ ኃይሎች ዱላ እና አስለቃሽ ጭስ መንገዳቸው መዘጋቱ ተገለጸ፡፡እሁድ ዕለት ከሆንዱራስ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ጎዳና ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታግደዋል። መንግስት “ሕገ ወጥ የጅምላ እንቅስቃሴን” አንቀበልም ሲል ገልጿል፡፡

ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከሆንዱራስ ወደ 7000 የሚገመቱ ስደተኞች ድህነትን እና ሁከትን በመሸሽ ወደ አገሪቱ ገብተዋል፡፡ ወደ ሜክሲኮ ቀጥሎም ወደ አሜሪካ ድንበር ለመጓዝ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡

በየአመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመካከለኛው አሜሪካ ስደተኞች “ካራቫን” በመባል በሚታወቁ ቡድኖች በእግር ጭምር በመጓዝ አሜሪካን ለመድረስ ይህን አደገኛ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡

ዲሞክራቱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕን ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ ለመለወጥ ቃል ገብተዋል፡፡ ሆኖም ረቡዕ ሥልጣን የሚረከቡት ባይደን፤ ፖሊሲዎች በአንድ ሌሊት አይለወጡም በማለት ስደተኞች ጉዞውን እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ቡድኑ ጓቲማላ ሲገባ ምን ተፈጠረ?

ስደተኞቹ ጓቲማላን አቋርጠው ወደ ሜክሲኮ ድንበር ሲጓዙ በደቡብ ምስራቅ ቫዶ ሆንዶ መንደር አቅራቢያ በፀጥታ ኃይሎች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ ተደርጓል፡፡

የተወሰኑ ወታደሮች እና የፖሊስ መኮንኖች መንገድ በመዝጋት ብዙዎቹን እንዳይንቀሳቀሱ አግደዋቸዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሁንም በኃይል ለማለፍ የሞከሩ ሲሆን በፀጥታ ኃይሎች ወደኋላ ተገፍተዋል፡፡ በርካታ ሰዎችም ቆስለዋል፡፡

ብዙ ስደተኞች ወደኋላ አፈግፍገዋል፤ የተወሰኑት ደግሞ አዲስ ሙከራ ለማድረግ በአቅራቢያው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በአቅራቢያው ወደሚገኙ ተራሮች ሸሽተዋል፡፡

የጓቲማላ ፍልሰት ድርጅት ኃላፊ ጊልርሞ ዳያዝዝ “እንደመታደል ሆኖ የፀጥታ ኃይሎች የመቋቋሚያ ዕቅድ አውጥተዋል። በዚህም ውጤታማ ሆነዋል” ብለዋል፡፡

ከጓቲማላን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በተሰጠ መግለጫ “የጓቲማላ መልእክት ግልፅ ነው። እንደዚህ አይነቶች ሕገ ወጥ የጅምላ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የላቸውም። ለዚህም ነው ከጎረቤት አገራት ጋር ይህንን ክልላዊ ጉዳይ ለመፍታት በጋራ የምንሰራው” ብሏል፡፡

ኋላ ላይ መንግሥት የህክምና እርዳታ የፈለጉ 21 ስደተኞች የኮቪድ-19 ምርመራ እንዳደረጉ አስታውቋል፡፡

ለምን ብዙ ሰዎች አሁን ይመጣሉ?

ስደተኞቹ በአገራቸው ስደት፣ ዓመጽ እና ድህነት የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ኅዳር ማዕከላዊ አሜሪካን በጎዶት ሁለት ግዙፍ አውሎ ነፋሶች የፈጠሩት ጥፋት ሁኔታዎች አባብሰዋል፡፡

እስማኤል ኤላዛር ለአሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገረው “አሁንም እዚያው ቦታ ጭቃ አለ። ሁሉም ነገር ተደምስሷል። ሁሉንም አጥተናል” ብሏል፡፡

ሆንዱራኖች ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ጉዞ ውስጥ በመሳተፍ ቫዶ ሆንዶ፣ ጓቲማላ ውስጥ ዕረፍት አድርገዋል። የተሻለ ሕይወት፣ ሥራን እና ደህንነትን ለማግኘት ወደ አሜሪካመሄድ ይፈልጋሉ፡፡

ከልጇ ጋር የምትጓዘው የ23 ዓመቷ ዳኒያ ሂንስትሮሳ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል እንደተናገረችው “ሥራም ሆነ ምግብ የለንም። ስለሆነም ወደ አሜሪካ ለመሄድ ወሰንኩ” ብላለች፡፡

የባይደን አስተዳደር አዲስ ፖሊሲዎችን ለመተግበር ቃል መግባቱ አንዳንድ ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ድንበር ለመድረስ ያነሳሳቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

BBC AMHARIC

Exit mobile version