Site icon ETHIO12.COM

አክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ጥር 20 እና 21 በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ብርሃነ የመማር ማስተማር ሂደትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ለመግለጫ ሰጥተዋል።

“በትግራይ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተቋርጦ የነበረው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ይጀመራል” ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገ ውይይት ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች የደህንነት ስጋት ሳይገባቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተመራቂዎቹ መገኘት እንዳለባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል። በቀጣይም ሌሎች ተመራቂ ላልሆኑ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የሚያስተምር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሰለሞን አብርሃም፤ መንግስት በትግራይ ክልል ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጉሎ እንደነበር አስታውሰዋል። በዋናነት በአክሱም እና በአዲግራት ዩኒቨርሰቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል እንዳልተቻለም አንስተዋል።

የመቐለ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ማስመረቃቸውን አስታውሰው፤ በአክሱም እና አዲግራት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥል የማመቻቸት ስራ መስራቱን ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version