Site icon ETHIO12.COM

ብልጽግና ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች ላይ ጠንቀቅ እንዲል አሳሰበ

ብልፅግና ፓርቲ ህብረተሰቡ ማንኛውንም ጉዳይ አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ትክክለኛነት በጥንቃቄ ማጣራት ይኖርበታል አለ ብልፅግና ፓርቲ፡፡ፓርቲው ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በመላው አለምም ሆነ በአገራችን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሃሰተኛ ወሬዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ ብሏል፡፡ማንኛም ዜጋ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን ከመቀበሉ በፊት ከተረጋገጠና ከትክክለኛ ምንጭ የተገኙ መሆናቸውን በጥንቃቄ ማጣራት አለበት ብሏል ፓርቲው፡፡

ከሰሞኑ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የሆኑትን የዶ/ር አብይ አህመድን ጤንነትና ደህንነት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም መሰረተ ቢስና ሆን ተብሎ ህብረተሰቡን ለማደናገር ሃላፊነት በማይሰማቸው አካላት የተሰራጨ ነውረኛ የሀሰት መረጃ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ህዝቡ ለወደፊቱም ከተመሳሳይ ሀሰተኛ ወሬዎች መጠንቀቅ ይኖርበታል ሲል አሳስቧል፡፡ህብረተሰቡን የማደናገርና ውዥንብር የመፍጠር ዓላማ ይዘው ሃሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ የሚያሰራጩ የጥፋት አካላትን በጥብቅ ተከታትሎ የህግ ተጠያቂ ማድረግ የመንግሥት ሃላፊነት ይሆናልም ብሏል፡፡

Exit mobile version