Site icon ETHIO12.COM

ልዩ ዜና – በትግራይ ሰላም አስከባሪ ለማስገባት የተያዘው ዕቅድ ሳይሳካ ቀረ፤ ስዬ ጦርነቱ አላለቀም አሉ

ኢትዮ 12 ዜና – በትግራይ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲገባ የተቀነባበረ ስራ ቢሰራም ሊሳካ እንዳልቻለ የኢትዮ 12 ዜና አቀባይ አስታወቁ። ዘመቻው በዋናነት በሚከፈላቸው በሚታወቁ ዓለም አቀፋዊ ሚዲያዎችና ግለሰቦች አማካይነት ሲካሄድ እንደነበር ተጠቁሟል። ስዬ አብርሃም ጦርነቱ እንዳላለቀ ገለጹ።

መንግስት “የህግ ማስከበር ዘመቻ ” ሲል በሚጠራው ግጭት በ100 ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት፣ ሚካናይዝድ ሃይል፣ ዘመናዊ መሳሪይ፣ ታንክ፣ አየር መቃወሚያና ሮኬት ታጥቆ ወደ ጦርነት የገባውን የትህነግ ሃይል በሁለት ሳምንት ውስጥ ሲረታ ጎን ለጎን የተጀመረው የሚዲያ ዘመቻ ለቅሶ እንደነበር የዜናው ባለቤት ይናገራሉ።

በህግ ማስከበሩ ዘመቻ እርምጃ የተወሰደባቸው የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ባለሙያ ሴኮ ቱሬ ” መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመን በ45 ደቂቃ ውስጥ ከጥቅም ውጪ አድርገነዋል” ያሉት የአገር መከላከያ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች በማፈግፈግ፣ ወደ ኤርትራ በመግባት አገግሞና ራሱን አደራጅቶ መልሶ በማጥቃት ፈጣን ድል ሲያስመዘግብ ወዲያውኑ የተጀመረው ዘመቻ ረሃብና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተከሰተ፣ ኤርትራ ወረራ አካሄደች የሚል ነበር።

የኤርትራ ሰራዊት በባድሜና ዛላንበሳ በኩል ድንበር ዘልቆ መግባቱን የትግራይ ተወላጆች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ዘረፋም እንዳካሄደ ይገልጻሉ። ዘመቻው ከተጠናቀቀ በሁዋላም ቀደም ሲል በነብረው ቂም መነሻ ምክንያት የሃይል እርምጃ እንደወሰደ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡም ነው።

ትግራይን ሲጠብቅ የነበረውን የአገር መከላከያ ” በመብረቃዊ ጥቃት ደመሰስነው” ሲሉ በአደባባይ የፎከሩ የትህነግ አመራሮች በሌላ አካል ስለመወረራቸው ሲናገሩ ለሰሚው ግራ እንደሆነ በመጥቀስ ” የራሳቸው ጉዳይ” ከሚሉት ጀምሮ የከፋ ወቀሳ እየተሰነዘረባቸው ነው።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ የማድረሱ፣ የኤርትራዊያን ስደተኞች ጉዳይ፣ የህጻናት ረሃብ እንዳሳሰበው በመግለጽ በተደጋጋሚ መግለጫ ሲያወጣ መቆየቱ ይታወሳል። እንደዜናው ከሆነ የተባበሩት መንግስታት ዛሬ ላይ በቂ ባይባልም ከዘጠና በመቶ በላይ መረጃ አግኝቷል። በትግራይ ከ85 በመቶ በላይ ማንኛውም ቦታ እርዳታ ያለ ችግር ማድረስ ይቻለል። ከከተማ ከተማ ዝውውር ሲደረግ የነበረው ፍተሻና ኬላ በአብዛኛው ተነስቷል። የድርጅቱ ሃላፊዎችም ትግራይን አይተዋል። የሚቀርቡት መረጃዎች የተጋነኑ እንደሆነ ግንዛቤ ተይዟል።

የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ዋና ጸሃፊውን ጨምሮ፣ የሃያላን አገር ባለስልጣኖች ጋር እጅግ ሰፊ ግንኙነት ከተደረገ በሁዋላ የመስክ ጉብኝት ሪፖርት ታክሎበት በትግራይ ሰላም አስከባሪ ሃይል ሊመደብ የሚችልበት አግባብ እንደሌለ ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ዘመቻው ቢሳካ ግብጽና ሱዳን የሰላም አስከባሪ ሃይል ለመላክ ቅድሚያውን ይዘው እንደነበር ይታወቅ እንደነበር ከሰማነው መረጃ ለማረጋገጥ ችለናል።

” ትግራይ እንደ ዳርፉር ተመስላ ሰላም አስከባሪ ቢመደብ ምን ይፈጠራል” በሚል የዜናው ባለቤት ለተጠየቁት ” ሰላም አስከባሪዎቹ ሱዳንና ግብጽ ናቸው። ሁለቱ ከሆኑ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ የተከሰተውን ሁሉ በማጋነን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሩጫ እንዳለ መግለሳቸው አይዘነጋም።

በዘመቻው እርምጃ የተወሰደባቸው የቀድሞ የረዥም ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን አስቀድመው የኤርትራ ሰራዊት የትግራይ ምድርን ከረገጠ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ ወዘተ ስም እየጠሩ የሚገቡ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አገሮች እንዳሉ መናገራቸው አይዘነጋም።

የሱዳን አሁን ላይ ድንበር ዘልቃ መግባት የሰላም አስከባሪ ጣልቃ እንዲገባ የተደረገው ጥረት በመክሸፉ ግብጽና የትህነግ ሰዎች ያዘጋጁት እቅድ ሁለት እንደሆነ ተመልክቷል። ዛሬ የመንግስት ባለስልጣናት በይፋ እንዳስታወቁት ሱዳን የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ሙሌት ከተካሄደ ነገሮች እንደሚበላሹ ወደማስፈራራት የሄደችው ሌሎች የመተናኮሻና የግብጽን እቅድ ማስፈጸሚያ አማራጭ ባለመኖሩ ነው። በስም በመጥቀስ “ሴራው የትህነግ ርዝራዦችና የግብጽ ግፊት ነው” ያሉት የመንግስት ሃላፊዎች አሁንም ቢሆን ትዕግስት እንደሚመርጡ እየገለጹ ነው።

“የትግራይ ሕዝብ ሁሉ ህወሃት ነው” በሚል የሽግግር መንግስት ረቂቅ ሰነድ ያዘጋጁት አቶ ልደቱ አያሌው በቅርቡ ከእስር ከተፈቱ በሁዋላ የትህነግ አፍቃሪ ተብሎ ከሚመደበው ርዕዮት ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሱዳን 40 ኪሎ ሜትር ዘልቃ ገብታ ህዝብ ዝም ማለቱ እንደገረማቸው ተናግረዋል። አያይዘውም ህወሃት ሲመታ ህዝብ ያሳየው ተነሳሽነት ሱዳን አገር ስትወር ዝም ከመባሉ ጋር ሲያነጻጽሩት እንደገረማቸው፣ መንግስት ወደ ጦርነት ገብቶ ድንበር ሊያስከበር እንደሚገባ ጠቁመው ነበር። ይህ አስተአየታቸው ጦርነቱ አሁን እንዲካሄድ ከተፈለገበት ምክንያት ጋር ሲሰላ የትህነግ አስተሳሰብ ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ ጦርነቱ የተፈለገው የተበተነውን የትህነግ ሃይል የመውጪያ ቀዳዳ ሰጥቶ ወደ ሱዳን እንዲያመልጥ ለማድረግ በመሆኑ ልደቱ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ምሁር ነኝ እያሉ ይህን ማለታቸው የተፈለገውን ዓላማ የመደገፍ እንደሆነ ምላሽ ተሰጥቷቸው ነበር።

የኢትዮ 12 የመረጃ አቀባዮች እንዳሉት ሁለት ከፍተኛ ጀነራሎች ኤርትራ ሄደው ነበር። የሄዱትም ተዘረፈ ስለተባለውና የኤርትራ ወታደሮችን አስመልክቶ የተነሳውን ቅሬታ እንደ ወዳጅ አጋር ለመወያየት ነበር። ከውይይቱም በሁዋላ ከመረጋጋቱ በፊት ከአንዳንድ አካባቢ ተወሰዱ የተባሉ ንብረቶች አንድ አካባቢ እንዲሰባሰቡ መደረጉን፣ እቃዎቹን ወስደዋል የተባሉ የሰራዊት አባላት መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ቀደም ሲል በባልደረቦቻቸው ” ሙሰኛ” ተብለው እስር ቤት ከወንድማቸው ጋር የቆዩትና በምህረት ተፈተው አንድነትን የተቀላቀሉት ስዬ አብርሃ ጦርነቱ እንዳላለቀና ትህነግ እንዳልተሸነፈ በሳምንቱ መጨረሻ በቨርቹዋል በተደረገ ውይይት ተናግረዋል።

ተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማይክ ራይነር ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት የህግ ማስከበር ዘመቻውን አሜሪካ ቀደም ብላ ጀምሮ ትደግፋለች። የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ የማንኛውም መንግሥት መብትና ግዴታ ውጤት መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ “የትግራዩ ጦርነት የተካሄደው የሃገሩን የግዛት አንድነትና የሕዝቦቹን ደሕንነት የመጠበቅ ግዴታ ባለበት የፌደራሉ መንግሥት እና ሕገ ወጥ በሆነ የትጥቅ አመጽ መካከል ባካሄደ ቡድን መካከል ነው” ሲሉ በስንብታቸው ማግስት ተናግረዋል።

ጦርነት በርካታ ውጥንቅጦች እንዳሉት ያወሱት ማይክ ራይነር ግድያዎችን ፣ የጾታ ጥቃቶችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ተጨባጭነት ያላቸው ሪፖርቶች ላይ በትግራይ እንደዚሁም መተከልን በመሳሰሉ ሌሎች ቦታዎች ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግም ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህ በንዲህ እንዳለ የኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን (UNHCR) ጋር በመሆን በትግራይ የሚገኙሁለት የኤርትራ ስደተኞችን ጎብኝተዋል። ስደተኞቹ በካምፑ ውስጥ ያለው ትምህርት መቋረጡ እና አንዳንዴ ምሽት ላይ ማንነታቸው ያልተገለጸ ሽፍቶች እየመጡ ያላቸውን እንደሚዘርፏቸው መናገራቸውን የ/UNHCR/ ተወካይ ሚስተር ክሪስ መልዘር ለቪኦኤ ለቪኦኤ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።

“ስደተኞችን እያፈኑ ወደ ኤርትራ እየወሰዷቸው ነው የሚለውን ክስ ግን በወሬ ደረጃ ብንሰማም ከስደተኞች ማረጋገጫ አላገኘንም ” ሲሉ ተወካዩ ከጉብኝቱ በሁዋላ ለቪኦኤ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በሀገሪቱ ከሚገኙ 1 ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች መካከል ችግር ያጋጠማቸው ኢምንት እንደሆኑ ገልጾ ለእነሱም መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እያሟላ መሆኑንን አመልክቷል። ይህ አንድ ታላቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።

በተደጋጋሚ እንደሚሰማው ትግሉ በሽምቅ ውጊያ መልክ እንደሚቀጥል፣ በቅርቡ ትግራይ ዳግም ” ነጻ” እንደምትወጣ ያገባናል የሚሉ ብወጭ አገር ያሉ የክልሉ ተወላጆች በስፋት እየገለጹ ነው። የስብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የሚጠቁሙ ሪፖርቶችን በማጉላት ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው። የኤርትራ ሰራዊት እንዳሸነፋቸው በመግለጽ የኢትዮጵያ መከላከያ ብቻውን ቢሆን ኖሮ ጭራሽ እንደማይችላቸው እያስታወቁ ነው። ደብረጽዮን በመጨረሻው አካባቢ ሆድ ብሷቸው ሲናገሩ ” አብይ በድሮን ጨፈጨፈን” በሚል ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ደጋግመው ማቅረባቸው አይዘነጋም።

Exit mobile version