Site icon ETHIO12.COM

ስዬ አብርሃ ቀጣዩ ትግል ” ራስን በራስ የማስተዳደር ነው፤ ጀግኖች ነን” አሉ፤ ንግግራቸውን ” ፎቶ ይዞ ማልቀስ” ሲሉ የተቹ አሉ

ባለፈው ሳምንት ለሟቹ አቶ ስዩም መስፍንና አቶ አባይ ጸሃዬ ሽኝት በሚል በስደት ያለው የትግራይ ሚዲያ ሃውስ የጋበዛቸው አቶ ስዬ አብርሃ ቀጣዩ ትግል ራስን እራስ የማስተዳደር እንደሆነ አመለከቱ። በንግግራቸው ባለስልጣን ያለበትን መኪና ለይቶ በሚመታ ድሮን ጭምር ጥቃት መሰንዘሩን አውግዘዋል። ይህን ንግግራቸውን የሰሙ የለውጡ ደጋፊ የትግራይ ተወላጆች ” ፎቶ ይዞ እንደማልቀስ ነው” ሲል ወርፈዋቸዋል።

የቀድሞውን የትህነግን ታሪክ በስፋት እያጣቀሱና እሳቸው የነበሩበትን ጊዜ በማንተራስ በህግ ማስከበሩ ዘመቻ እርምጃ ተውሰዶባቸው ህይወታቸው ያለፉትን እነ አቶ ስዩምና አባይ ጸሃዬን በማንሳት ” ጀግኖች ናቸው” ያሉት ስዬ አብርሃ፣ እሳቸው ትህነግ ያልተሸነፈ፣ የጀግኖች ድርጅት እንደሆነ አስታውቀዋል።

” አረቦችና የኤርትራ ሰራዊት ተባብረው አጠቁን” ሲሉ የተደመጡት ስዬ አብርሃ እሳቸው የመከላከያ ሚኒስቴር ሆነው ሲመሩት ስለነበረው ተቋምና ሰራዊት በግፍ በተኛበት ስለመረሸኑ ያሉት ነገር የለም። በጥያቄ መልኩም አልቀረበላቸውም።

” በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ” አሉ ስዬ ሃዘን፣ ንዴትና ቁጭት በሚነበብበት ፊት፣ ” ለመጀመሪያ ጊዜ ባለስልጣን ያለበትን መኪና ለይቶ በሚመታ ድሮን ጥቃት ተሰንዘረብን፣ ተደበደብን” ሲሉ ድጋፉን የአረብ አገሮች እንደሆነ አመልክተዋል። እስራኤል በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥቃት ስለመፈጸሟ ዓለም ሲዘግብ እንዳልሰማ ሆነው ይሁን በሌላ ባይታወቅም ኢትዮጵያ ድሮን መጠቀሟን ለማመን ተችገረዋል።

ስዬ ከወራት በፊት መቀለ ሆነው በዚሁ ሚዲያ ቢሮ እየተዝናኑ፣ እረፍት በሚሰማው መንፈስ ስለ ትግራይና ህወሃት የጦርነት ብቃት ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል። ቀደም ሲል ወይም ድሮ ” ጦርነትን እንሰራዋለን” ማለታቸው እንዳለ ሆኖ በዚሁ በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ” ብርጌድ አፍርሰን ብርጌድ መገንባት፣ መካናይዘድ ሃይል አፍረሰን መካናይዝድ ሰራዊት መገንባት እናውቅበታለን” ሲሉ ጠያቂዋ በስሜት ትንቆራጠጥ ነበር።

ማብራሪያቸውን በስሜት ሲተርኩ የነበሩት ስዬ ” ጦርነትን ስለምናውቀው እንፈራዋለን፤ ከገባንበት ግን እንደምናሸንፍ እናውቀዋለን” ያሉት ስዬ ያልጠበቁትን ውጤት መመዝገቡን ልክ ለመቀበል የተቸገሩ ይመስላሉ። ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶክተር እንዳልካቸው ሃይለ ሚካኤል በቀጥታ ለአቶ ስዬ ባይሆንም በጥቅሉ እንዲህ ያለ ስሜት ላላቸው ” ልክ እንደ ለቅሶ ነው፤ ሃዘን ቀስ እያለ እንደሚረሳው” ሲሉ ከማህበራዊ የስነልቦና ሃቅ አንጻር እንደሚታይ አስታውቀዋል።

የለውጡ ደጋፊ የትግራይ ተወላጆች በበኩላቸው የአቶ ስዬን አስተያየት ” ፎቶ ይዞ እንደማልቀስ ነው” ሲል ወርፈዋቸዋል። ስዬ ትህነግን እዋጋዋለሁ በሚል ከአንድነት ፓርቲ ጋር ተቀላቅለው እንደነበር አመልክተዋል።

ስዬ ቀጣዩ ትግል ራስን በራስ የማስተዳደር እንደሆነ ሲናገሩ ቀደም ሲል እንደሚባለው ታላቋን ትግራይ በሁለት አገራት ፍርስራሽ ላይ ለመገንባት የተጀመረውን ውጥን ማስቀጠል ይሁን ሌላ ይፋ አላደረጉም። ቀደም ሲል ኢትዮጵያንና ኤርትራን አፍርሶ ” አባይ ትግራይ”ን ለመግንባት እቅድ ተያዞ ይሰራ እንደነበር በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።

Exit mobile version