Site icon ETHIO12.COM

በጉለሌ እጽዋት ፓርክ ውስጥ የተነሳው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ጉለሌ እጽዋት ፓርክ ውስጥ እሳት ተነስቶ በተደረገው ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳያስከትልና ወደ ሌላ ቦታ ሳይስፋፋ በቁጥጥር ስር መዋሉን ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ፓርኩ ለከተማዋ ውበት እና ድምቀት መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ አዲስ አበባን ከጎርፍ ለመከላከል ከሚጠቅሙ ስፍራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።እሳቱን ለማጥፋት በርካታ የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች፣ የሠራዊቱ አባላት፣ የአዲስ አበባ የእሳት እና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባልደረቦች፣ የመንገዶች ባለስልጣን፣ የአከባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውም ነው የተገለፀው።

ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ በእሳት ማጥፋቱ ሥራ ላይ ርብርብ ላደረጉ አካላት በአስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለእሳቱ መነሳት ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ቀሪ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚከናወኑ እና መረጃዎችንም በየወቅቱ ለኅብረተሰቡ እንደሚያደርሱ ገልፀዋል።

Exit mobile version