Site icon ETHIO12.COM

ጠላት አይኑን የጣለበትና ያንሰራራው የማዕድን ወጪ ንግድ

ኢትዮጵያ ወርቅ፣ፕላቲኒየም፣ኒኬልና ታንታለምን የመሰሉ የማዕድን ሃብት እንዳላት በታሪክ የሚታወቅ ቢሆንም የማዕድን ዘርፉ ግን ገና ብዙ እንዳልተሰራበትና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳልሆነ ከኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ ግዚያት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እ.ኤ.አ በ2014 ሃገሪቱ ከማዕድን የወጪ ንግድ 541 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያገኘች ቢሆንም እ.ኤ.አ ከ2015 አስከ 2019 ባለው ግዜ ውስጥ ከማዕድን የወጪ ንግድ የሚሰበሰበው ገቢና ለዓመታዊ የተጠራ ሀገራዊ ምርት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እየቀነሰ ስለምጣቱ ይኸው መረጃ ይጠቁማል።

እ.ኤ.አ በ2013/14 የዘርፉ ዓመታዊ እድገት 3 ነጥብ 2 ከመቶ ነበር። እ.ኤ.አ በ2014/15 ግን ወደ 25 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል። ይሁን እንጂ በዚሁ አልቀጠለም። ይልቁንም አሽቆለቆለ እንጂ። እ.ኤ.አ በ2015/16 ወደ 3 ነጥብ 3 በመቶ መውረዱ በመረጃው ተመላክቷል።

እ.ኤ.አ በ2016/17 29 ነጥብ 8 ከመቶ፣እ.ኤ.አ በ2017/18 ደግሞ 20 ነጥብ 8 በመቶ እንደነበር የጠቀሰው መረጃው እ.ኤ.አ በ2018 የማዕድን ዘርፉ ለዓመታዊ የተጠራ ሀገራዊ ምርት ያለው አስተዋፅኦ እ.ኤ.አ በ2013 ከነበረው 9 ነጥብ 1 ከመቶ ወደ 1 ከመቶ ማሽቆልቆሉን አመልክቷል። በ2011/12 ከማዓድን ዘርፉ ከ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 618 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን መረጃው ጠቅሷል።

ሃጋራዊ ለውጡን ተከትሎ የማዕድን ዘርፉ ለሃገሪቷ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግና የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

Read this- ኢትዮጵያ ወርቅ እንዳትሸጥ ዘመቻ ተጀምሯል፤ ኢትዮጵያዊያን ለእርስ በርስ ሽኩቻ ትኩረት ሰጥተዋል

በዚህም መነሻነት በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወር ከማዕድን ወጪ ንግድ   በተለይ ደግሞ ከወርቅ ማዕድን ከፍተኛ ገቢ መገኘቱን ነዳጅና ማዕድን ሚንስቴር አስታውቋል።

የነዳጅና ማዕድን ሚንስቴር ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክ ተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ፍቃዱ እንደሚገልፁት ከማዕድን ወጪ ንግድ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ወርቅ ቢሆንም እምነበረድ፣ የከበሩ ማዕድናትና ሌሎች የኮንስትራክሽን ማዕድናት በወጪ ንግድ ውስጥ የተካተቱ የገቢ ማስገኛ ምንጮች ናቸው። በዚሁ መሰረትም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር ውስጥ ከአጠቃላይ የማዕድን የወጪ ንግድ 339 ነጥብ 5 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ለውጭ ገበያ ከቀረቡት ማዕድናት ወርቅ 335 ነጥብ 54 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስገኘት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል። ኤመራልድ፣ ሳፋየርና ኦፓል ከተሰኙ የከበሩ ማዕድናት የወጪ ንግድ ደግሞ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።

ለኮንስትራክሽን(ግንባታ) ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ገበያ የቀረቡ በመሆናቸው በወጪ ንግዱ ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ ጋር የሚጠቃለል እንዳልሆነ ወይዘሮ ፍሬህይወት ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ የወርቅ ማዕድንን የብሔራዊ ባንክ ገዝቶ ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ሌሎቹ የከበሩ ማዕድናት ግን በአብዛኛው የላኪነት ፍቃድ በተሰጣቸው ድርጅቶች አማካኝነት ወደ አውሮፓ፣እስያና አሜሪካ ሃገራት ይላካሉ። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር የወጪ ንግዱ ሲነፃፀር የአሁኑ የስድስት ወር አፈፃፀም በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ትግራይ ክልሎች የወርቅ ማዕድን ወደ ብሔራዊ ባንክ በመላክ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

የከበሩ ማዕድናትን በተለይ ኦፓል ለውጪ ገበያ በማቅረብ ደግሞ የአማራ ክልል ሰፊ ድርሻ ይዟል። ሳፋየርና ኤመራልድ ማዕድናትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል ተጠቃሽ ነው። የባለፈው ዓመት የአንድ ዓመት የወጪ ንግድ አፈፃፀም 207 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አካባቢ ነበር።

ሆኖም በዘንድሮው በጀት ዓመት በስድስት ወር ብቻ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል። በስደስት ወር ብቻ የ 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ልዩነት እንዳለውም አመልክተዋል።

ከማዕድን የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ከፍ ሊል የቻለውም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋን በማሻሻሉ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ሌላው የዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ መጨመር ለወጪ ንግድ ገቢው ከፍተኛነት አስተዋፅኦ አድርጓል። የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲቀንስ የተሰሩ ስራዎችም ለገቢው ማደግ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። በዚህ በኩል የተሰራው ሥራ በሰዎች እጅ ያሉ ወርቆች በተለይ በድምበር አካባቢዎች በአብዛኛው ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገቡ ለማድረግ አግዟል።

ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ከወርቅና ከሌሎች የማዕድን ሃብቶች ወጪ ንግድ አሁን ከተገኘው በላይ ገቢ ለማግኘት የዕቅድ ክለሳ በማድረግ ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል። በተለይ ደግሞ ከወርቅ ውጪ ባሉ ሌሎች የከበሩና ከፊል የከበሩ ማዕድናት የወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ እንዲያስገኙ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ለዚህም የማዕድን እምራቾችንና ገዢዎችን የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት በመገንባት ላይ ናቸው።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ ከክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር፣የክትትልና ድጋፍ ስራዎችንም በማከናወን በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከመቼውም ጊዜ እየተንቀሳቀሰ ነው። የተዘጉ የወርቅ ኩባንያዎችን ለመክፈትም በሂደት ላይ ይገኛል። እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች ከወርቅ ማዕድን የወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል የበለጠ ያግዘዋል።

አስናቀ ፀጋዬ አዲስ ዘመን ጥር 24/2013


Exit mobile version