Site icon ETHIO12.COM

ለክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ የምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም ሊዘጋጅ ነው

ለክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ የምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።የቢሮው ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራሙ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣አድናቂዎቹ እና የአርቲስቱ ወዳጆች በተገኙበት ይካሄዳል፡፡

መርሃ -ግብሩም አርቲስቱ ከ60 ዓመታት በላይ ለኦሮሞ ኪነ-ጥበብ እድገት ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጨምረው ተናግረዋል።በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።

በወቅታዊ ክስተቶች ሳይሸነፍ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት እንደሚያደርገውም አውስተዋል።መርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣አድናቂዎቹ እና የአርቲስቱ ወዳጆች በተገኙበት እንደሚካሄድም ተገልጿል።ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው መርሃ ግብርም የአርቲስቱ የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎች ላይ የተፃፈ መጽሐፍ እንደሚመረቅም ነው የተናገሩት።

ክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የተመሰረተውን የመጀመሪያው የኦሮሚኛ ቋንቋ የኪነት-ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው።አርቲስቱ ከኦሮሚኛ በተጨማሪ፣በሱማሊኛ፣በአፋርኛ፡በሐረሪ፣በአማርኛና በሱዳን ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።

( ኢዜአ)

Exit mobile version