Site icon ETHIO12.COM

” ከ 27 ዓመታት የልማት ዘፈንና ፉከራ በኋላ የትግራይ ህዝብ በችግር ላይ ወድቆ መገኘቱ አሳፋሪ ነው” አቶ አንዳርጋቸው

በ27 ዓመታት የልማት ዘፈንና ፉከራ በኋላ የትግራይ ህዝብ በችግር ላይ ወድቆ መገኘቱ አሳፋሪ እንደሆነ የኢሳት ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አመለከቱ ። ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው ክልል ሲመራ የነበረው የህውሓት ቡድን መሆኑን አስታወቁ።አቶ አንዳርጋቸው በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከ27 ዓመታት ዘፈንና ፉከራ በኋላ የትግራይ ህዝብ በምግብ እህል እንኳን ራሱን ባልቻለበት ሁኔታ የምግብ እርዳታ ተቀባይ ሆኖ ማየት እጅግ አሳፋሪ ነው።

ክስተቱ ቡድኑ 27 ዓመታት በሙሉ በበላይነት ኢትዮጵያን በገዛበትና ባስተዳደረበት ወቅት ማንኛውንም ነገር ያደረገው ለራሱ ጥቅም እንደሆነ የትግራይ ህዝብ ከተጨባጭ የዛሬ ህይወቱ እንዲያስተውል እድል እንደሰጠው አስታውቀዋል።

“ቡድኑ በመላው አገሪቱ የዘረፈውን ሀብት በጣም ጥቂት ለሆኑ የራሱ የቅርብ ሰዎች ብቻ መጠቀሚያ አድርጎት እንደነበር አሁን ያለው ሁኔታ በገሃድ አሳይቷል” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ፣ ሲፈጽሙት የነበረው ወንጀልም ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበረው ማየት እንዳስቻለ ገልጸዋል ።

“የትግራይ ህዝብ እንደ 27 ዓመቱ ከዘፈን፣ ፋከራና ቀርቶ ልማት ውጭ ሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ያገኙትን የፖለቲካ ነፃነት የተነፈገ ነው ። ህዝቡ ይህንን ጠንቅቆ ያውቀዋል” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ፣ ይህም ቡድን የሚመራበት መንገድ እጅግ ኋላቀር እንደነበር እንደሚያሳይ አመልክተዋል ።

ከህግ ማስከበር ዘመቻ በፊት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የክልሉ ህዝብ በሴፊቲኔት ሲረዳ ነበር ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ፣ ከዚህ በተጨማሪም በቀጥተኛ እርዳታ የሚኖረው ህዝብ ቁጥርም ቀላል እንዳልነበር አስታውቀዋል። በዋነኛነት ያጋጠመው የምግብ እህል እጥረት ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ህዝቡ ሊረዳው እንደሚገባ አመልክተው ፤

” መንግስት ተደራርበው ለህዝቡ የከበዱትን ችግሮች ግምት ውስጥ አስገብቶ በተቻለው መጠን እና ፍጥነት ህዝቡ የረሃብ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ማድረግ። ህዝቡ በመድሃኒት እጥረት ችግር እንዳያጋጥመው አስፈላጊውን ነገር በፍጥነት ማቅረብ ይጠበቅበታል። ከዚህም መንግስት የተቻለውን ያህል እያደረገ ነው” ብለዋል ።

አሁንም በተበጣጠሰ መልኩ በየጎሮኖውና በየጥሻው የተደበቁ የጁንታው ርዝራዞች የመንግስት ጥረት በተሟላ መንገድ እንዳይከናወን እያደረጉ ናቸው። ምግብና መድሃኒት የጫነውን ተሽርካሪ ሞት አፋፍ ላይ ለደረሰ ለገዛ ወገናቸው እንዳይደርስ ለማድረግ የሽብር ወሬ እየነዙ እንደሆነ አመልክተዋል ።በእንዲህ አይነት ሁኔታ አስቀድመንም ያለፍን በመሆኑ መንግስት ይህን ሁኔታ እልህ አስጨራሽ እንደሚሆን አውቆ እራስን ማዘጋጀት ይኖርበታል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ፣ መንግስት መስራት ያለበትን ነገር ከመስራት ውጪ ምንም ሌላ አማራጭ እንደሌለው አስታውቀዋል። ኢዜአ

Exit mobile version