የትግራይ “አባቶች “ና የአባ ማቲያስ ትህነግን ነጻ የማውጣት ፖለቲካ በጌታቸው ምላስ

ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ መቀሌ “ይቅርታ” ለመጠየቅ አቅንተው “በትግራይ ሕዝብ የደረሰው መከራና ግፍ በአለም ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ነው” አሉ። አክለውም በዚሁ ትግራይ ላይ ተፈጸመ ባሉት ግፍ እጅጉን ማዘናቸውን ተናገሩ። “ስላላገዝናችሁ ወይም ስላልደረስነላችሁ እጅጉን ይሰማናል” ሲሉ ሃዘናቸውን በገሃድ ገለጹ። ለተጎዳ ማዘነ የአንድ የዕምነት አባት ተግባር ቢሆንም የሳቸው ሃዘን ግን ትህነግን ከሃጢያቱ ለማንጻት ከትግራይ የእምነቱ አባላት ጋር የተያዘ ተመሳሳይ አቋም ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ፣ ዕምነቱን አክባሪ፣ እንደ መሪዎቹ ክርስቶስን በየቀኑ የማያሳዝን፣ በመሆኑ ፓትሪያርኩን ተቀበለ እንጂ እንደ እውነቱማ እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊመሩ፣ በክብሯ ዙፋን ላይ ሊቀመጡ ቀርቶ ደጁም ዘንድ መድረስ የማይገባቸው ካድሬ ነበሩ። ሱዳን ሆነው ለወያኔ ሲሰሩ፣ ከዛው ከሱዳን በሚተላለፍ የትግል ሬድዮ ሲሉ የነበሩትን፣ እንዴትና እንደምን ሆነው እዚህ ወንበር ላይ እንደወጡ መለስ ብሎ የዩቲብ መረጃዎችን የሚያገላብጥ የሚመስክረው የአደባባይ የቅርብ ጊዜ ሃቅ ነው። እናም ሕዝበ ክርስቲያኑ አቡነ ማቲያስን እንደ አባት የሚቆጥራቸው ስለማያውቃቸው አይደለም። እሳቸውም ይህንኑ ያውቁታል።

የትግራይ “የዕምነት አባቶች” አሁን ድረስ ኩርፊያ ላይ በመሆናቸው ሊያናግሯቸው የሄዱትን የዋናው ኦርቶዶክስ ጳጳስና አጋሮቻቸውን እንዳላገኙ ሰማን። ዕርቅ በጎ ነገር ነውና ትግራይ ድረስ ለይቅርታ መሄድ የመንፈሳዊው መንገድ መርህ ነውና ይበል ቢያሰኝም፣ ይህን ያህል የትግራይ አባቶችን ያስኮረፈው ምን ይሆን በሚል ለተፈጠረብኝ ጥያቄ አቶ ጌታቸው መልስ ሰጡኝና ብዕሬን አነሳሁ።

ቅድሚያ ማሳሰቢያዬ

የእምነቱ አባል ባለመሆኔ የስም፣ የአሰያየምና አንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ግድፈት ባነሳ ቅድሚያ ይቅርታ ይደረግልኝ። በተጨማሪ አንባቢያን ቅዱስ መጽሃፉ እንደሚለው እውነት አርነት ያወጣልና የሃሳቡን እውነታዊ ጭብጥ ላይ አተኩሩልኝ። የማነሳው የአሳብ ፍልሚያ በአብዛኛው የቀናት የወራት፣ ቢበዛ የሁለትና ሶስት ዓመታት ወይም አራት ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ጉዳዮች ላይ ነውና ብዥታ ይኖራል ብዬ አላምንም። የቆየ ታሪክ ሳይሆን በአይን ብረታችን፣ በራሳችን ጆሮና ስሜት የተረዳነው፣ ያየነውንና የሰማነውን ሲተውኑ የነበሩት ተዋናዮችም የማይዘነጉ በመሆኑ ይህን ስጽፍ ብዙም ጥንቃቄ ማድረግ አልፈለኩም። የማነሳው ማሳያ ጥያቄዎችን ብቻ በመሆኑ አንባቢያን በረጋ መንፈስ ጉዳዮቹን በልቷቸውና የራሳችሁ አቋም ያዙ!! እዚህ ላይ የትግራይ ህዝብ “ሰላማዊው”ማለቴ ነው የደረሰበት ስቃይ አሁን ድረስ ያሳዝነኛል። ልክ እንደ አማራና አፋር ህዝብ!! ግን ለዚህ ስቃይና ግፍ የዳረገውን ትህነግን አዝሎ መኖር መምረጡ ደግሞ ” ይህ ህዝብ ምን ነክቶት ነው? ምን እስከሚሆን ነው የሚጠብቀው?” እንድል እገደዳለሁ።

አይ ሚዲያዎቻችን ስል አነባሁ፤ አይ ሰበር ዜናዎች ዛሬም ጌታቸው ረዳን ይጠቅሳሉ

ወደ ዋናው አሳቤ ሳልገባ ሚዲያዎች “ሰበር” እያሉ አቶ ጌታቸው ረዳን ሲጠቅሱ ባላዝንም እጅግ ገርሞኛል። ሲጀመር የትግራይ አባቶች አሉት የተባለው ዜና በዜና ደረጃ ይመጥናል ወይ? ለያውም “እስኪ አቶ ጌታቸው ያሉትን እንስማ” በሚል አዲሱን መልዕክታቸውን ሳይቆርጡ ሲቀሰቅሱላቸው ነበር። አቶ ጌታቸው “እምነት አለኝ” ሲሉ ራሳቸውን ፈርሃ አምላክ ካላቸው መድበው ለህልውናቸው የታገሉትን ኢትዮጵያዊያን ተለሳልሰው በዕምነት አባቶች ስም ተከልለው አዲስ ፕሮፓጋንዳ ሲረጩ የማይረዳ ሚዲያ ያሳዝናል።

ሳይገባቸው፣ እንዲገባቸውም ሳይጨነቁ ለመከረኛ ሳንቲም ለቀማ ተኩለው ማታ ብቅ የሚሉት፣ ነገሩ ገብቷቸው ሆን ብለው የሚያቶሰቱሱት ተከፋዮች ጌታቸው ረዳን ጠቅሰው ዜና ሲሰሩና ሰበር ሲሉ ያሳምሙኛል። አቶ ጌታቸው ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ ትህነግ የጀመረውን ራሱን ነጻ የማድረግ ቅስቀሳ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለሚያሰራጩ የመከላከያን በክህደት መቀላት ላስታውስ እወዳለሁ። ሴት የመከላከያ አባላት ጡታቸው መቆረጡን ዳግም እንድትፈትሹ አሳስባለሁ። አቶ ጌታቸው እንዴትና በምን ያህል ርቀት በመከላከያችን ላይ ይዛበት እንደነበር፣ እንዴት ኢትዮጵያን እያራከሰ የፈጠራ ውርጅብኝ ያወርድባት እንደነበር ላፍታም ቆም ብላችሁ እንድትገመግሙ አሁንም ማስታወቅ እፈልጋለሁ።

See also  "ልጆቻችን የት ናቸው?" የትህነግ አዲሱ ፈተና "ግፋ በለው" ሲሉ የነበሩ ሚዲያዎች የከበሩበት፣ የድሃ ልጆች ያለቁበት...

ትህነግ “ሂዱና አማራን ዝረፉ፣ ግደሉ፣ አውድሙ …” ብሎ እንደላካቸው የገለጹ ምን እንዳደረጉ፣ በወረራ የፈርሰውንና የወደመውን፣ የተገደሉትና ቤታቸው ድረስ እየመጡ የዘረፏቸውን የአፋርና የአማራ ህዝብ ምን እንደደረሰበት አስቡና ይህ ሁሉ ሲሆን አቶ ጌታቸው መን እያሉ ይዛበቱ እንደነበር ከመዜው ተረስቶ ነው እንደዚህ ዓይነት መርከስ የተመረጠው? ለትግራይ ንጽሃን ማሰብና መቆርቆር ለዜና ቢበቃም እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉትን ህሊና ቢስ ካድሬዎች በዚህ ደረጃ ማስተጋባት ምን የሚሉት ኢትዮጵያዊነት ሊሆንስ ነው? ከሆነም ሚዲያው አቶ ጌታቸውን ገልጦና ገላልጦ ማቅረብ በተገባ ነበር።

አቶ ጌታቸው የዛሬ መሪ፣ የትናንት የጦርነት አፈ ቀላጤ

አቶ ጌታቸው የትግራይ አባቶች ስለተቀየሙበት ጉዳይ ካነጋገሯቸው በሁዋላ የተረዱትን ሲያብራሩ “የእኛም አቋም ነው” በሚል ነበር። በአፈ ቀላጤነት ዘመናቸው እንደዛ ሲቀደዱ የነበሩ ካድሬ ይህን ሲሉ “ስምንተኛው ሺህ” ከማለትና ከማለፍ ውጪ ምን ይባላል? ከትግራይ አባቶች ጋር ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ላለፉት ሶስትና ሁለት ዓመታት ያለ ልዩነት መክረማቸውን ያስረዱት አቶ ጌታቸው ማብራሪያቸውን ሲጀመሩ ቀደም ሲል የሰላም ሚኒስቴር ለክልሉ ደብዳቤ በመጻፍ የእምነት አባቶቹ ተገናኝተው እንዲወያዩ ጥሪ ማቅረቡን ገለጹ። ” ለምን ያ መንገድ እንደተመረጠ አልገባኝም” ሲሉ ካድሬነታቸው መዘዙና የቀድሞ አፈ ቀላጤ ሆኑ። ሲያጠቃልሉ ጣልቃ የመግባት አሳቡም ፍላጎቱም እንደሌላቸው፣ ሊሆንም እንደማይገባ አመላክተው ሲጀምሩ ሁለት መነጋገር ያቆሙ አካላትን “እናቀራርብ” ብሎ መጠየቅን ውግዝ አስመስለው ከሳሉ በሁዋላ ራሳቸው ከዚህ መስሉ አካሄድ ነጻ አወጡ። መቼም ካድሬ ሲባል መስቀል የያዘውም ያልያዘውም ልዩነት የላቸውም። ጳጳሱም በስውር ለነጭ ቃለ ምልልስ እየሰጡ “ስለ ትግራይ እንዳላለቅስ እንዳልተነፍስ ታፍኛለሁ” በሚል ኢትዮጵያ ላይ ሸምቀቆ የሚያጠብቁ ክህነታቸው በካድሬነት የተጎናጸፉ አይደሉምን?ወደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ ላምራ።

የትግራይ አባቶች የትግራይ ህዝብ ሁለትና ሶስት ዓመት የውጭ ሃይል ሳይቀር ጣልቃ ገብቶ በጦርነት ያንን ሁሉ መከራ ሲያይ፣ በችግር ሲሰቃይ፣ በመቶ ሺህዎች ሲያልቅ፣ ከፍተኛ ግፍ ሲደርስበት፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተክርስቲያን ድምጿን እንዳላሰማች ለአቶ ጌታቸው አስረድተዋል። ልብ በሉ። ማን ነበር የጦርነቱ አክተር? ማን ነበር “በባህርዳር ወይስ በደብረ ብርሃን በኩል አዲስ አበባ እንግባ፣ እጅህን ለትህነግ ስጥ” እያለ የኢትዮጵያን ጀግኖች እያራከሰ የትግራይን ተወላጆች እድሜና ጾታ ሳይመርጥ ሲማግድ የነበረው? ይቀጥላሉ አቶ ጌታቸው ” ይህ የነሱ ብቻ ሳይሆን የእኛም አቋም ሆኖ የቆየ ነው” ብለዋል። አይ አቋም። አጭር ሚሞር ያለው ሚዲያና የሳንቲም ቅንጫቢ ያሰከረው የማህበራዊ ሚዲያ መንጋ ካለ የፈለጉትን ለማሰራጨት ምን ችግር አለ!!

ቅዱስ ፓትሪያርኩና አንዳንድ ያሉዋቸው አባቶች በግላቸው ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። ከጳጳሱ ጋር ተጠቃቅሰዋል። እዚህ ላይ “ቅዱስነታቸው ስለምን ለአማራና አፋር ህዝብ አልተሟገቱም?” የሚለውን ጥያቄ እንተወውና ለማን ነበር መግለጫ የሰጡት? እሳቸው መግለጫ የሰጡት ነጭ ትግራይ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር የሳተላይት ስልክ ይዞ የዓለም የምግብ ድርጅት መኪና ዘንድ ቆመው ጦርነት ሲመሩ ገሃድ መሆኑን ለምናውቅ የአቶ ጌታቸው የግል ምስጋና መነሻና መድረሻው ግልጽ ነው። እንቀጥል። ባለካባው ካድሬ ነገ የሚያስከትለውን ጥሪ በጉጉት እንጠብቅ። “እሳቸውን ብቻ እንሰማለን” በሚል ለጊዚያዊ ትርምስ ስትደግፉ የነበራችሁ፣ የትግራይ አባቶች ኩርፊያ መጨረሻ ወልቃይት ጠገዴ እንደሆነ አስቀድሜ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። መንግስት እንዲያደራድር ይደረግና ይህ ጥያቄ በኦርቶዶክስ ስም ይቀርባል። ይኸው ነው። እነ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ድግፋችሁን አጠንክሩ። አሁን መስመሩ ተሰምሯል።

See also  ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በቢሮው አስቀምጦ የተገኘው ተከሳሽ በ13 ዓመት ፅኑ እስራና በ75 ሺህ ብር አንዲቀጣ ተወሰነበት

የትግራይ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ” ጥፋትን ከመደገፍ ያልተናነሰ አቋም ይዛለች” ሲሉ ቅሬታቸውን እንደገለጹ አቶ ጌታቸው በለስላሳ ድምጽ አውግተውናል። ይህም ጉዳይ የዕምነቱን አባቶች አቋም እንደሸረሸረው መረዳትና ቢዘገየም ይህን የሚመጥን ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። “የሚመጥን” ሲሉ ምዕራብ ትግራይን መልሱ ስለመሆኑ አሁንም ደግሜ እነግራችኋለሁ “ጳጳሱ ወይም ሞት” ስትሉ የነበራችሁ በአማራ ስም የምትጮሁ የተልባ ስፍሮች በሉ ድግፋችሁን ቀጥሉዋ!!

የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ አባቶችን እንደጠላ ማን ይናገርለት?

በርዕስ ደረጃ አሳቡ ጠጣር ይመስላል። ግን እውነት ነው። አቶ ጌታቸው ” ቤተክርስቲያን ጥፋትን ከመደገፍ ያልተናነሰ አቋም ይዛ ነበር” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ገልብጠን እንየው። የትግራይ አባቶች በአቶ ጌታቸው አንደበት “ጥፋት” ብለው የፈረዱት የኢትዮጵያ ህዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ የመከተውን ወረራ መሆኑንን ልብ ይሏል። ይህ አቋምና ቅስቀሳ ትህነግ ወገቡ ተቀንጥሶ በበቃኝ የሰላም ፊርማ ካኖረ በሁዋላ ላስፈጀው ህዝብ “ራሳችንን ነው የተከላከልነው” በሚል የጀመሩትን የቆርጦ ቀጥል ፕሮፓጋንዳ ማስደገፊያ ነው። ኩርፊያውም ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ የማይሆነው ለዚህ ነው። ብታምኑም ባታምኑም የኩርፊያው ዓላማ ይህና ይህ ነው። አንድ ሚሊዮን ወጣት አስጨርሶ በሃይማኖት ስም ሌላ ድራማ!! ሌላ አውዜን!!

ለውጡ ይፋ እንደሆነ ትህነግ ወደ ትግራይ የበረረው ማን ሂድ ብሎት ነው? ከ1997 ምርጫ ውጤት በሁዋላ አቶ መሰስን ጨምሮ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር “እኛ ከሄድን ኢትዮጵያ ሶማሌ ትሆናለች፣ ትበታተናለች፣ ኢንተርሃሞይ ይሆናል፣ ጦራችንን ይዘን ወ ትግራይ እንሄዳለን” እያሉ በገሃድ ግብር ከፍለን ባቆምነው ቴሌቪዥን ይነግሩን እንደነበር እዚህ ላይ ማስታወስ እወዳለሁ። ዝርዝሩን ከፍለጋችሁ ወመዘክር ሂዱና የዛን ሰሞን የታተመ ሪፖርተርን አንብቡ።

ኢትዮጵያ እንድትበተን ተደርጋ በመሰራቷ፣ ቅጥ ያጣ የጥላቻና የልዩነት መርዝ ሲረጭባት በመቆየቷ ነበር ” እሳትና ጭድ እንዴት ይስማማል” በሚል የዛሬው የትግራይ መሪ አቶ ጌታቸው አማራና ኦሮሞ ሚና ለይቶ ከመገዳደል ይልቅ አንድ ላይ ሆኖ ትህነግን ማነቃነቁ አበሳጭቷቸው “ጋኔኖች” ሲሉ የተሳደቡት። ሳንቲም የማያደርገው ነገር የለምና ይህ ሁሉ ተረስቶ ዛሬ እኚህ ሰው ” ሰበር ዜና” ሆኑ።

ወደ ትግራይ አባቶች ሳመራ እነዛ እናቶች “የሰላም ያለህ “ብለው በትግራይ መሪዎች እግር ላይ ሲንደባለሉ የት ነበራችሁ? እላለሁ። ትህነግ በዕበልት አብጦና “ማን ካለ እኔ፣ እኔ የጦርነት ባለሟል፣ ጦርነት ባህሌ..” እያለ ሩብ ሚሊዮን ሃይል ሲገነባ ምን እያደረጋችሁ ነበር? ትግራይ ህጻናት ክላሽ እየያዙ እንዲፎክሩ ሲደረግ፣ እንሳሳ ውሻ፣ አህያና ፈረስ በቀለም እያጌጡ ፣ ጎዳና ሙሉ የጦርነት አዋጅና ነጋሪት ሲመታ የትኛው ሪፖብሊክ ነበር የምትኖሩት? ውድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይላችን ሁለት አስርት ዓመት ትግራይን ሲጥበቅና ሲያለማ እንዳልነበር በድንገት በክህደት ሲታረድ፣ በክህደት የታረዱት ወግኖች እንደ ባዕድ በምርኮ ተይዘው በሰልፍ ሲተፋባቸው የት ነበራችሁ? በሲኖ ትራክ ሲዳመጡ የት ነበራችሁ? ሴቶች እህቶቻችን መሳሪያ ፈተው በቃላት ለመናገር የሚቀፍ ግፍ ሲፈጸምባቸው አልሰማችሁም?

ይህ አልተፈጸመም የሚል መከራከሪያ የሚያቀርብ አንድ የትህነግ ካድሬም ሆነ ደጋፊ የለም። አቶ ሴኮ ቱሬ በኩራት በደቂቃዎች ውስጥ ከጥቅም ውጭ አድርገናቸዋል ሲሉ ነግረውናል። ተገደው ነው እንዳይባል እዛው መቀሌ ሆነው የተናገሩት የ”ድል” ዜና ነው። ቆይቶም ሌተና ጄነራል ጻድቃንም በቃለ ምልልሳቸው ለታሪክ ይመች ዘንድ በድጋሚ ምስክር ሆነዋል። “ነገሩ አልቋል ከአሁን በሁዋላ ከማን ጋር ነው የምንነጋገረው? የሳምንታት ጉዳይ ነው” በማለት ድል ሲያበስሩ ኩርፊያ ስለሚያስከትለው የመልስ ምት ማንም ያሰበ አልነበረም። እንኳን የትህነግ ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው አለቆቻቸውም አልገመቱትም ነበር።

የትግራይ አባቶችን የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ይጠይቃቸዋል። ቀደም ሲልም እስር ቤት ሁሉ የኦሮምኛ ቋንቋ መማሪያ ሲሆን፣ እናት ልጇ አስከሬን ላይ እንድተቀመጥ ተደርጎ ስትወገር፣ የቡድን ዝርፊያ ሲፈጸም፣ ጥላቻ በገሃድ ትህነግ ጓዳ እየተመረተ ሲረጭ ” ተዉ በትግራይ ህዝብ ስም አታድርጉ” አላላችሁም። ያ ሁሉ ሰራዊት ተደራጅቶ ሲርመሰመስ ድል እንጂ ሌላ ጉዳይ ሊታያችሁ ባለምቻሉ ሌላውን ህዝብ ” ስራህ ያውጣህ” በማለት ዳግም አራት ኪሎን ስትማትሩ እንደነበር የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቃል። እናንተም ታውቃላችሁ። የፈሲታ ተቆጢታ እንዲሉ ዞራችሁ ማኩረፋችሁ አስገራሚ ሌላ ታሪክ ነው።

See also  ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ሰርቀዋል የተባሉ ሃላፊዎች ላይ ፍርድ ተሰጠ

እናንተ ለሰላም አስቀድማችሁ ብትቆሙና “ሃዋፘዊ” ስራ ብትሰሩ ኖሮ የትግራይ ህጻናት አያልቁም። የትግራይ ህዝብ በዚህ ደረጃ አይጎዳም። አማራና አፋር ክልል እንደ ባዕድ ተወሮ ማቅ አይለብስም ነበር። መከላከያ ባይታረድ ኖሮ አንድም የሻዕቢያ ሃይል የትግራይን መሬት አይረግጥም ነበር። እናም ኩርፊያችሁ ያስደንቅ ካልሆነ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም። ከዚህም የከፋ የታሪክ ዕዳም መሸከማችሁን አትዘንጉ። ይልቁኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ማቅ ለብሳችሁ ይቅርታ በሉት። የትግራይን ህዝብ ጭምር። ከትህነግ ስር አትርመጥመጡ።

አቶ ጌታቸውም በጮሌነት ሌት ተቀን ሃሰትና ቅጥፈትን እያሰራጩ ነው። ከተረፉ በሁዋላ ማታ ማታ በዙም፣ ቀን ቀን በየአዳራሹ እያሉ ያሉት ነገር በህግም የሚያስጠይቅ ነው። “ሃይሎጋ” እያሉ ያስጨረሱት የትግራይ ህዝብ ሳይቆጫቸው ዛሬ ዳግም በካድሬ ካባ መርዝ መርጨት ላይ ተጠምደዋል። የተደጋገመ የቪዲዮ መረጃም አለ ቢያቆሙ ይሻልዎታል። የትግራይ አባቶችም እስኪ ወልቃይት ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ምን እንድተፈጸመ መርምሩና መቅደሳችሁ ግብታችሁ ምከሩ። የትግራይ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እስከዛሬ ከካድሬ ቂጥ ቂጥ ስር በመሮጥ እምነትን ያረከሳችሁ አባቶች ራሳችሁን መርምሩ። ምስኪኑን ህዝብ በስቀልና በቅዱሳን ስም ወደ ጥፋት አትንዱ።

ሳጠቃልለው

አቶ ጌታቸው ወደዚህ ሃላፊነት ከመጡ በሁዋላ አዲስ አበባና ትግራይ፣ በዙምና በመድረክ የሚዘባርቁትን ጉዳይ መንግስት ሊያርቅ ይገባል። አሁን አፈር ቅመው ከተነሱ በሁዋላ እርድታ እርዳታውን ላፍ እያደረጉ “ራስን የመከላከል ስራ ነው የሰራነው” በሚል የጀመሩት ቅስቀሳና “መሳሪያ አላስረከብንም ዝም በሉ፣ ሙያ በልብ ነው” የሚል ጮሌነት ወደ ሚፈለገው ግብ አያደርስም። ሌሎችንም ለእርቅና አብሮ ተሳስቦ ለመኖር አያነሳሳም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አብሮነት ሲሰብኩ እሳቸው “ሙያ በልብ ነው” የሚል ዘመቻ ላይ የተጠመዱበትን ምክንያት መንግስት አስጠርቶ ሊጠይቃቸው ይገባል። የትግራይ አባቶችም ቢሆኑ ራሳቸውን ችለው የመለየት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሚዲያ ፊት በመውጣት ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መስልስ እንዲሰጡ ሚዲያዎች ግፊት ማድረግ ይጋባቸዋል።

ጦርነቱን ትህነግ እንደጀመረው ምንም ጥርጥር የውም። ከላይ እንደተባለው ራሳቸው መስክረዋል። ጀግኖቻችን ሲሉ ደጋፊዎቻቸው ዜናውን በሰበር ተቀባብለው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተዛበቱበት መረጃ አየሩን የኦላው ስለሆነ ብዙ ማለት አይስፈልግም። ይሁን እንጂ ጦርነት አውዳሚ፣ ገዳይና ለመከራ የሚዳርግ በመሆኑ በትግራይ ህጻናት፣ አዛውንትና ጎልማሶች ላይ የደርሰው ጉዳት እጅግ ከሚያሳዝናቸው መካከል መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። የዚህ ጉዳት ጠባሳ በቀላሉ የሚለቅ እንዳልሆነም አምናለሁ። እናትና ባቶች እርሻ ላይ ሲውሉ፣ ጎልማሶች አካለ ጎዶሎ ሆነውና ሞተው ቤተሰቦቻቸውን ሲያጎድሉ ማየት ልብ ያደማል። ይህ እንዲሆን ያቀዱ፣ የቀሰቀሱ፣ የሃሰት ትርክት ሲቀልቡና እሳቱን ሲቆሰቁሱ የነበሩ ዳግም “እኛም ተቀይመናል” ሲሉ ምስማት ግን ድጋሚ የሞቱትን ምስኪኖች ቀስቅሶ እንደገና የመግደል ያህል ሆኖ ይሰማናል። እናም ይህን ነጭ እውነት በመዘርዘር “የትግራይ አባቶች ትህነግ በግፍ ባህር ሲዋኝ፣ መከላከያ ሲታረድ አማራና አፋር ሲወረር የት ነበራችሁ ?” ቢል መልሳችሁ ምን ይሆናል? እስኪ ያገባናል የምትሉ አድሙት።

በትረ ሰለሞን – ጎማ ቁጠባ

Leave a Reply