Site icon ETHIO12.COM

“የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አብሮነቱን ማሳየት አለበት” ዶክተር ሙሉ

የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን እገዛ በማድረግ አብሮነቱን ማሳየት እንዳለበት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገለጹ።ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ጨምሮ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከሁሉም የእምነት ተቋማት ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና ከኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጋር ዛሬ በመቀሌ ተወያይተዋል።

በውይይቱም በትግራይ ክልል የገጠመው ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታና ሕዝቡ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ የሃይማኖት አባቶቹ ተናግረዋል፡፡የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሠብዓዊ ድጋፍ ለሕዝቡ በፍጥነት ለማድረስ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለማስፈንና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኘነቱን ለማጠናከር ጊዜያዊ አስተዳደሩ እየሰራ ያለውን ተግባርም እንዲሁ።የሕዝቡን ስነ ልቦና ለማጠናከር የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም በውይይቱ ላይ ገልፀዋል፡፡የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት አባላት በበኩላቸው በክልሉ ሠራተኞች ሠርተው እንዲገቡ፤ ገበሬው ወደ ሥራው እንዲመለስ ዘላቂ ሠላም መስፈን እንዳለበት ተናግረዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ ሰብዓዊ ድጋፎች በአግባቡ ለሕዝቡ መድረስ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።በክልሉ የፈራረሱ የመንግስት መዋቅሮችን መልሶ ለመገንባት በተለይ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት እንዳለበትም የአገር ሽማግሌዎቹ አስገንዝበዋል፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የፌዴራል መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።”ሰብዓዊ ድጋፉ አልደረሰም ተብሎ የሚወራው ፍፁም ሃሰት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ማዕከል በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ዶክተር ሙሉ “የትግራይን ሕዝብ አሁን ካለበት ችግር ለማውጣት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል” ብለዋል።የትግራይ ሕዝብ አሁን ካለበት ችግር እንዲወጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በማገዝ አብሮነቱን ማሳየት እንዳለበትም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።በመቀሌ ለሁለት ቀናት ቆይታ የነበራቸው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ውይይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

Exit mobile version