Site icon ETHIO12.COM

የአ/አ/ከ/አስተዳደር መሬት ‹‹በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከተሰጠው አካል ፈቃድ ውጭ ለመያዣነት አያገለግልም››

የአ/አ/ከ/አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በሚሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ ካርታው ‹‹በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከተሰጠው አካል ፈቃድ ውጭ ለመያዣነት አያገለግልም›› የሚል ማሳሰቢያ ማስቀመጡ ከንብረት መብት አንፃር ያለው ህጋዊነትና ፋይዳው


ውድ የፌስ ቡክ ገጻችን ተከታታዮች በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፌዴራል ህጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ጥናት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ከላይ በርዕሱ ላይ በተመለከተው ጉዳይ ዙሪያ የስራ ክፍሉ ያዘጋጀውን አጭር ሀተታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

የአ/አ/ከ/አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የነባር ባለ ይዞታነትና የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ፣ የነባር ይዞታ ተነጻጻሪ ካርታ፣ ግንባታው የተጠናቀቀ የሊዝ ይዞታና የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ (አረንጓዴ ቀለም ያለው)፣ የሊዝ ተነጻጻሪ ባለይዞታና የቤት ባለቤትነት ካርታ እና ግንባታው ለተጀመረ የሊዝ ባለይዞታነትና የቤት ባለቤትነት ካርታ (ቢጫ ቀለም ያለው) ተራ ቁጥር ላይ ለተዘረዘሩት የካርታ አይነቶች በጀርባቸው ላይ የተቀመጠው ማሳሰቢያ ‹‹በዚህ ካርታ ላይ የሰፈረው ቦታ/ይዞታ በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከተሰጠው አካል ፍቃድ ውጭ ለመያዣነት አያገለግልም›› ሲል በነባር ይዞታ ተነጻጻሪ ካርታ ላይ ግን ‹‹በዚህ ካርታ ላይ የሚገኝ ንብረትን በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከተሰጠው አካል እውቅና ውጭ ለመያዣነት አያገለግልም የሚል ይዘትን አስቀምጧል፡፡ ይህም ካርታን ለመያዣ ለመጠቀም የሚመለከተውን አካል ፍቃድ ማግኝት ወይስ ማሳወቅ ብቻ በቂ ነው? ይህ የሚያስፈልገውስ ለይዞታው ብቻ ወይስ ካርታው ላይ ለሰፈረው ለማንኛውም ንብረት ነውን ? ለሚለው ጥያቄ ወጥ በሆነ መልኩ ምላሽ የማይመልስ፣ የተለያየ ይዘት ያለው ማሳሰቢያ በተለያየ ጊዜ በካርታዎች ላይ የሚቀመጥና በተጠቃሚዎች ላይም የተለያየ ግዴታ እና መብት የሚጥል መሆኑን ያመላክታል፡፡

የዚህን ማሳሰቢያ ህጋዊነትና አላማን በተመለከተ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ጽ/ቤት ህጋዊ አስተያየት እንዲሰጠበት በጠየቀው መሰረት ካርታውን የሚያዘጋጀው የአ/አ/ከ/አስ/መ/ል/ማ/ቢሮ በቀን 27/02/2011 በቁጥር ይአሰ/45/2011 ማብራሪያ ሲሰጥ ካርታን እንደመያዣ መጠቀም የሚችሉት ከብሄራዊ ባንክ በኩል እውቅና ያገኙ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ መሆናቸውን፤ ከግለሰብ ጋር ለሚደረግ የብድር ውል ግንኙነት ካርታን ማስያዝ እንደማይቻል፤ ለዚህ የህግ መሰረቱም የይዞታ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 12/2004 አንቀጽ 33 መሆኑን፤ ‹‹በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከተሰጠው አካል ፍቃድ ውጭ ለመያዣነት አያገለግልም›› በሚለው ማሳሰቢያ ውስጥ ስልጣን የተሰጠው አካል ማለት የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገ/ፕ/ጽ/ቤት እንደሆነና ከዚህ አካል ፍቃድና እውቅና ውጭ ለየትኛውም አገልግሎት ካርታን መጠቀም እንደማይችል፤ የማሳሰቢያው አላማም ብሄራዊ ባንክ እውቅና ከሰጣቸው ተቋማት ውጭ ንብረትን በመያዣነት እየያዙ ብድርን ለመስጠት የሚንቀሰቀቀሱ ተቋማትንና አራጣን ለመከላከል የተቀመጠ አሰራር እንደሆነ አብራርቷል፡:

በየካርታዎች ላይ የተቀመጠው ማሳሰቢያ ይዘትና የተሰጠውን ማብራሪያ ይህ ሲሆን የማይንቀሳቀስ ንብረትን አጠቃቀም ከሚደነግጉ አለማቀፋው እና ሃገራዊ ህጎች ጋር ያለው ተስማሚነት እስከ ምን ድረስ ነው?፤ የማሳሰቢያውና የአሰራሩ ምንጭ በትክክልስ መመሪያ ቁ.12/2004 ሊሆን ይችላል? በንብረት የመጠቀም መብት ላይ ገደብ የሚያስቀምጥ ከመሆኑ አንጻር በህጎች ላይ የተቀመጠውን የገደብ አጣጣል መርህ የተከተለ ነው? ፤ በማብራሪያው እንደተቀመጠው ማሳሰቢያውና አሰራሩ አራጣን የመከላከል ሚና አለው? ይህስ ተግባር የሚያከናውን ሌላ ተቋም የለምን? የመመሪያ ቁ.12/2004 አንቀጽ 33 ድንጋጌ ይዘት ፈቃጅ ወይስ ከልካይ? ይህ አንቀጽስ በውል የሚቋቋም የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መለከታል? የሚለውን መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ የንብረት መብት ህገ-መንግስታዊ እውቅና ሊሰጣቸው ከሚገባ መብቶች አንዱ እንደመሆኑ መጠን የ1987ቱ የኢትዮጲያ ህገ-መንግስትም በምዕራፍ ሶስት ለሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነጻነቶችን እውቅና የሰጠ ሲሆን ማንኛውም የኢትዮጲያ ዜጋ ጉልበቱን ፤ የመፍጠር ችሎታውን እና ካፒታሉን ፈሰስ አድርጎ ያገኘው ንብረት ላይ የግል ባለቤትነት መብቱ የተጠበቀና የመሽጥ፤የማውረስና በማንኛውም መልኩ የማስተላለፍ (በዋስትና የማሳዝ) መብት ያለው መሆኑን ደንግጓል፡፡ ይህ መብቱ ሊገደብ የሚችለው የሌሎችን መብት ከተቃረነ ወይም መገደቡ የህዝብ ጥቅምን ለመጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ባለ መብቱ ለሚደርስበት መጉላላት በቂ ካሳ ከተከፈለው እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

መሬትን በተመለከተ የባለቤትነት መብቱ የመንግስትና የህዝብ ሲሆን ከገጠርና ከኢንቨስትመንት መሬት በተቃራኒ የከተማ መሬትን እንዴት ማግኝት ይቻላል? ይህ ህገ-መንግስት ከመውጣቱ በፊትም ሆነ በኋላ የከተማ መሬት የያዙ ሰዎች መብት እስከምን ድረስ ነው? የሚለውን ግን ሳይመልስ አልፎታል፡፡ የ1952ቱ የፍትሐብሄር ሕግ ህገ-መንግስቱ ከመወጣቱ በፊት እንደመውጣቱ መጠን የማይንቀሳቀስ ንብረትን (መሬትን ጨምሮ) መሸጥ፤ መለወጥ፤ማከራየት እና ለብደርም ሆነ ለሌላ እዳ እንደመያዣ መጠቀም እንደሚቻል በዝርዝር ደንግጓል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በሶስት መልኩ ማለትም በህግ፤ በፍርድ ቤትና በውል ሊቋቋም ይችላል፡፡ ከህግ የሚመነጭ መያዣ ከተዋዋይ ወገኖች መካከል አንዱ ወገን ግዴታውን ባይወጣ ሌላው ወገን ጥቅሙን ስለሚያስከብርበት መንገድ ሳይዋዋሉ በቀሩ ጊዜ ህጉ ክፍቱን ለመሙላት ያሰቀመጣቸው ሁኔታዎች ሲሆኑ ለምሳሌ አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሸጠ ሰው ላልተከፈለው የብር መጠንና በውሉ ላይ ላሉት መብቶች የሸጠው የማይንቀሰቀስ ንብረት እንደ መያዣ ሆኖ ያገለግለዋል ሲል ህጉ ደንግጎ ይገኛል፡፡ በፍርድ ቤት ከሚሰጡ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች የሚመነጭ መያዣ የሚቋቋመው ከፍርድ በፊትም ሆነ በኋላ በራሱ በፍርድ ቤቱ አነሳሽነት ወይም በከሳሹ (በፍርድ በለመብቱ) ጠያቂነት ለክርክሩ መነሻ የሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት ክርክሩ እስከሚያልቅ ድረስ ወይም ለፍርድ አፈጻጸም ሲባል እንደመያዣ ሆኖ ተከብሮ እንዲቆይ ሲል ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ በውል የሚቋቋም የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ተዋዋይ ወገኖች ነጻ ፍቃድና ስምምነት መሰረት በተደረገ ወይም ለወደፊቱ በሚደረግ ውል ለሚደርስ /ይደርሳል/ ተብሎ ለሚጠበቅ የብር መጠን ልክ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንደ መያዣ የሚያዝበት ተጨማሪ ውል ነው፡፡
ስለውል በጠቅላላው በሚደነግገው ክፍል የተቀመጡ የችሎታ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ባለእዳው አንድን የማይንቀሳቅስ ንብረት ለገንዘብ ጠያቂው በውል በመያዣነት ለመስጠት የሚችለው ንብረቱን የመሸጥ የመለወጥ መብት ካለው ወይም ሶስተኛ ወገንም ከሆነም ንብረቱን ስለባለዕዳው ለማሲያዝ የሚችለው ንብረቱን በስጦታ የመስጠት ችሎታ ያለው ከሆነ ብቻ ነው፡፡

የፍትሐብሄር ህጉ የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ ውል የሚቋቋምባቸው ንብረቶች በህግ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የሚቆጠሩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንደተጠበቁ ሆነው መሬትና ቤት ናቸው ቢልም አሁን መሬት የህዝብና የመንግስት ከመሆኑ አንጻር በቀጥታ ያለምንም ገደበ መሽጥ ወይም መለወጥ አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን የከተማ ቦታን በሊዝ ያገኘ ግለሰብ ለቦታው በከፈለው የሊዝ ዋጋ ልክና የሊዝ ዘመን ድረስ ቦታውን ወይም ቤቱን ለውል ማሳዣ መጠቀም እንደሚችል በሊዚ አዋጅ 721/04 ተደንግጓል፡፡ ይህንንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ሊዝ አፈጻጸም ደንብ ቁ.49/2004 እና መመሪያ ቁ.11/2004 በተመሳሳይ በግለጽ ደንግገውት ይገኛል፡፡

ለብድር ሆነ ለሌላ ውል ማስያዣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲያዝ ውል ለማረጋገጥና ለመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው አካል (በአዲስ አበባ ደረጃ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኢጀንሲ) ቀርቦ በጹሁፍ ሆኖ መመዝገብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ያስፈለገበት ምክንያት በዋናነት የዜጎችን የግል ንብረት የማፍራት፣ የመጠቀም እና በሕጋዊ መንገድ የማስተላለፍ መብትን በማስከበር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማገዝ የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ፤ የመልካም አስተዳደርን እና የነጻ ገበያ ሥርዓት ግንባታን ለማሳለጥ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ሰነድ አረጋጋጩም ሰነድ ከማረጋገጡና ከመመዝገቡ በፊት የሰነዱ ይዘት ሕግን እና ሞራልን የማይቃረን መሆኑን የማረጋገጥ ስልጣንና ተግባር ያለው ሲሆን የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ ውል በአዋጁ መሠረት ሲመዘግብ በሕግ አግባብ የተዘጋጀ የመያዣ ውል ሰነድና የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ሁለት የሰው ምስክር መቅረቡን፤ እዳና እገዳ አለመኖሩን፣ ተዋዋዮች ከህግ ወይም ከውል የመነጨ ስልጣን ያላቸው ስለመሆኑ፣ የተዋዋዮች መታወቂያና ያላገባ ወይም ያገባ ማስረጃ፤ የትዳር አጋር የፈቃድ ስምምነት፣ በመያዣነት የቀረበው ንብረት የባለቤትነት ማረጋገጫ ማስረጃ አስቀርቦና መርምሮ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህም ተበዳሪውም ሆነ አበዳሪው እንዳይታልልና ህግ-ወጥ ተግባር ውስጥ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ከህግና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚመነጭ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በውልና ማስረጃ ቀርቦ መረጋገጥና መመዝገብ አይጠበቅበትም ምክኒያቱም ከህግ ከሆነ ህጉን ጠቅሶ መብትን ማስከበር ስለሚቻል እንዲሁም ከፍርድ የመነጨ ከሆነም የማይንቀሳቀስ ንብረት አስተዳዳሪ ለሆነ አካል ንብረቱ እንዲታገድና ተከብሮ እንዲቆ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረግ ብቻ በቂ ስለሆነ ነው፡፡ በተመሳሳይም ከባንክ ወይም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ለሚደረግ የብደር ውል የማይንቀሳቀስ ንብረቱን እንደመያዣ የሰጠ ተበዳሪ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ሄዶ መዋዋልና ማስመዝገብ ሳያስፈልገው ንብረት አስተዳደር ለሆነው (በአዲስ አበባ ደረጃ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ) አካል የብድር ስምምነቱና የመያዣ ውሉ በባለንብረቱ የግል ማህደር ተመዝግቦ እንዲቀመጥ መድረጉ ብቻ በቂ መሆኑ በህጎች ላይ እና በቃለ -መጠየቅ ከሰበሰብነው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዚህም ምክኒያት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚጠይቁ ባለጉዳዮችን ከሊዚ አዋጁ፤ ከደንቡና ከአፈጻጸም መመሪያው ጋር የተጣጣመና ወጥ የሆነ አገልግሎት ለመስጠጥ ያስችለው ዘንድ የይዞታ አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁ.12/2004 ያወጣ ሲሆን ይህ መመሪያም በከተማ አስተዳደሩ የሚኖሩ ነዋሪዎች የካርታ ይሰራልኝ፤ የስም ይዛወርልኝ፤ ይዞታ ይከፈልልኝ እና ተያያዥ አገልግሎትን ምን ሲያሟሉ ያገኛሉ የሚለውን አስከ አንቀጽ 32 ድረስ ካስቀመጠ በኋል ዋስትናና እገዳ ይመዝገብልኝና ይሰረዝልኝ አገልግሎት እንዴት ይሰጣል? የሚለውን በአንቀጽ 33 ምላሽ የሰጠ ሲሆን የዚህ አገልግሎት ጥያቄ ቀጥታ ከነማን ሊቀርብ ይችላል የሚለውን በማሳያ መልኩ ሲደነግግ ‹‹የዋስትናና ዕገዳ ምዝገባ አገልገሎት ጥያቄ ከፍርድ ቤት፣ ከባንክ፣ ከኢንሹራንስና ሌሎች በሕግ አግባብ ስልጣን ከተሰጣቸው አካላት ሊቀርብ ይችላል።

“ዋስትናና ዕገዳ ምዝገባና ስረዛውም እንደሚከተለው ይፈጸማል›› በማለት አስቀምጦ እናገኝዋለን፡፡ በየካርታዎች ላይ እየተቀመጠ ያለው ማሳሰቢያና ካርታን እንደማስያዣ በመጠቀም ከግለሰብ መበደርን የሚከለክለው አሰራር የህግ መሰረቱ መመሪያ ቁ.12/2004 ነውን? የሚለውን ጉዳይ ስንመረምረው ከላይ ከተቀመጡት አለማቀፍ ህጎች፤ የ1987ቱ ህገ-መንግስት፤ የፍትሃብሄር ህጉ፤ የሊዚ አዋጁና በአዲስ አበባ ደረጃ የወጡ የሊዚ አፈጻጸም ደንብና መመሪያም ሆነ ራሱ መመሪያ ቁ.12/2004 በነባር ይዞታ ሆነ በሊዚ ለተገኘ ቦታ የተሰጠን ካርታ ባለይዞታው ለብደርም ሆነ ለሌላ ውል እንደማሳዣ ለመጠቀም የሚችለው በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል ሲፈቅድና ውሉም (የብደር ውልን ጨምሮ) ከብሄራዊ ባንክ እውቅና ካገኘ የፋይናንስ ተቋም ጋር ከተደረገ ብቻ ነው የሚል ቅድመ-ሁኔታን ያዘለ ገደብ /ክልከላን/ አላስቀመጡም፡፡ ይልቁንም ከላይ እንዳየነው በአለማቀፍ ህጎችና ስምምነቶች ላይ የተቀመጡ የሰብአዊ መብት (የንብረት መብትን ጨምሮ) ድንጋጌዎች ሲተረጎሙ መንግስትም ቢሆን መብቶችን በሚያጣብብና በሚያፈርስ መልኩ ሊተረጉሟቸው እንደማይገባ ተደንግጓል፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስትም ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት የስምምነት ሰነዶች ልክ እንደ ሀገሪቱ ህግ የሚቆጠሩ ሲሆን ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮችም እነዚህን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና የማሳደግ (የማሟላት) ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ህገ-መንግስቱ በዚህ መልክ ለንብረት መብት ጥበቃ የሚያደርግለት ከሆነ በየደረጃው የሚገኝ ህግ አውጭ፤ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ ለአሰራር አመችነት ሲል ወይም በቸልተኝነት በግልጽ የህገ-መንግሰት ወይም ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎችን መሰረት (ድጋፍ) ያላደረገ ህግ በማውጣት፣ የህግ መሰረት የሌለው አሰራር በማስቀመጥና በአግባቡ የወጡ ህጎችንም ከወጡበት አላማ ውጭ በመተርጎም መብቶችን መገደብ ወይም ማስቀረት የህግ ውጤት የሌለውና እንዳልተደረገ የሚቆጠር ተግባር እንደሆነ ህገ-መንግስቱ ደንግጓል፡፡

የፌዴራሉ የሊዚ አዋጅም ሆነ የአ/አ/ከ/አስተዳደር ያወጣው የሊዚ አፈጻጸም ደንብና መመሪያ ካርታን ለማሳዣነት ለመጠቀም በህግ ስልጣን የተሰጠው አካል ፍቃድ ያስፈልጋል፤ ይህ ስልጣን የተሰጠው አካልም የአ/አ/ከ/አስ/የይ/ጊ/ሽ/አገ/ፕሮጀክት ዴስክ ስለመሆኑም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ማረጋገጫ ካርታን ከግለሰብ ጋር ለሚደረግ የብድር ውል መጠቀም አይቻልም የሚል የህግ ድንጋጌ አላስቀመጡም፡፡ የአግልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁ.12/2004 በመግቢያው ላይ ‹‹ሰነድ ያላቸው ህጋዊ ባለይዞታዎችና በህግ የከተማ ቦታ የሚፈቀድላቸው ሰዎች የሚጠይቋቸውን የተለያዩ መስተንግዶዎች ከሊዚ አዋጁና ደንቡ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመስጠት እንዲቻል›› በማለት ያስቀመጠውን አለማ ስናይም የሊዚ አዋጁን፣ የአፈጻጸም ደንብና መመሪያውን ሳይከተል ለተቀመጠ ማሳሰቢያና አሰራር የህግ መሰረቱ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንስ ከመመሪያው ስያሜ ማለትም (የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ) ከሚለው ጀምሮ ከአንቀጽ 1 አስከ 32 ያሉ የህግ ድንጋጌዎች የካርታ አሰጣጥ፤የስም ዝውውር፤ የቦታ ክፍፍል የመሳሰሉት አገልግቶች በተገልጋዩ በሚጠየቁ ጊዜ እንዴት ይስተናገዱ የሚለውን እንደሚመልሱት ሁሉ አንቀጽ 33 ትም ከላይ እንዳየነው ፍርድ ቤቶች፤ባንኮች እና የኢንሹራንስ ተቋማት የማይንቀሳቀስ ንብረትን (ካርታን) ለፍርድ አፈጻጸምም ሆነ ለእዳ ማስከበሪያ ሲይዙ በውልና ማስረጃ መዋዋልና ማስመዝገብ ስለማያስፈልጋቸው ቀጥታ ንብረቱን ለሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እግዱ ወይም የዋስትና ሰነዱ በባለ እዳው የግል የንብረት ማህደር እንዲቀመጥ ወይም እዳና እገዳው እንዲነሳ አግልግሎት በሚጠይቁበት ጊዜ አግልግሎቱ እንዴት ይሰጣል? የሚለውን ለመመለስና ይህን አገልግሎትስ እነማን ያገኛሉ ለሚለው በአብነት መልክ ያስቀመጠ እንጅ ካርታን የሚይዙት እነዚህ አካላት ብቻ ናቸው ባላለበት፣ መመሪያ እንደመሆኑ መጠን የፍትሃብሄር ህጉንና የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አዋጅን መሻር በማይችልበትና በነዚህ ህጎች መሰረት በግለሰቦች መካከል ለሚቋቋም የብደር ውል ማስከበሪያ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣን በግልጽ ባልከለከለበት፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ማረጋገጫ ካርታን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ለአ/አ/ከ/አስ/የይ/ጊ/አገ/ፕ/ዴስክ ስልጣን ባልሰጠበት ሁኔታ የመመሪያው አንቀጽ 33 በካርታዎች ላይ ለሚቀመጠው መብት ገዳቢ ማሳሰቢያና ከግለሰብ ጋር ለሚደረግ የብድር ውል ካርታን እንደ ማሳዣ መጠቀምን ለሚከለክለው አሰራር የህግ መሰረት የሚሆንበት አግባብ የለም፡፡

የማሳሰቢያውና የክልከላው አላማም ባለይዞታዎችን በብድር ስም ካርታን እንደመያዣ እየያዙ የአራጣን ስራ ከሚሰሩ ግለሰቦች ለመጠበቅና አራጣን ለመከላከል ነው ይባል እንጅ አራጣ ማለት አንድ ሰው የሌላውን ሰው ችግረኛነት፤ የበታችነት፤ ወይም ደካማነቱን አይቶ በህግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ካበደረው ወይም ተመጣጣኝነት የሌለውን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ቃል(ውል) ያስገባው እንደሆነ ነው፡፡ ከጉዳያችን ጋር የሚያያዘው ተመጣጣኝ ያለሆነ (ከእዳው የበለጠ) ንብረት በመያዣ መያዝ ሲሆን ይህ ድርጊት በወንጀል የሚያስቀጣና በቀጥታ የፍትህ አካለት (የፖሊስ፤ የዓቃቤ ህግ መሰሪያ ቤትና የፍርድ ቤትን) የሚመለከት ከመሆኑ በተጫማሪ አበዳሪው ተመጣጣኝ ያልሆነ ንብረትን (መሬትና ቤት ሲሆን) በምትኩ እንዲሰጠው የሚያደርግ አሰገዳጅ ቃል (ውል) ተበዳሪውን ለማሰገባት ከላይ እንደተመለከትነው ይህ የተገባው ቃል ወይም ውል በውልና ማስረጃ መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ መዝጋቢው አካልም (በአ/አ/ ደረጃ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኢጀንሲ) ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መካከል የተዋዋዮችን ችሎታ ፤ ንብረቱን ወይም ካርታውን የሚያስዘው ግለሰብ ህጋዊ ባለቤትነትን፤ ንብረቱ ለምን ያህል የገንዘብ መጠን እንደተያዘ በውሉ መቀመጡን፤ ይህን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ከህግና /ለምሳሌ አራጣን ከሚከለክለው የወንጀል ህግ/ ከሞራል አንጻር የማይቃረን መሆኑን የማረጋገጥና የመመዝገብ ነው፡፡

ወንጀልን የመከላከል የሁሉም ግለሰብና ተቋም ድርሻ ቢሆንም በዋናነት ከላይ የጠቀስናቸው ተቋማት ሃላፊነት ሆኖ እያለ በህግ በግልጽ ይህን ወንጀል እንዲከላከል ግዴታ ባልተጣለበትና በካርታ አጠቃቀም መብት ላይ ገደብ የማስቀመጥ ስልጣን ባልተሰጠበት ሁኔታ አራጣን ለመከላከል ነው በሚል የዜጎችን በንብረት የመጠቀም ሰብአዊ መብት የሚገድብ የህግ መሰረት የሌለው ማሳሰቢያና ከልካይ አሰራር ማስቀመጡ አግባብ አይደለም፡፡

ውድ የፌስ ቡክ ገጻችን ተከታታዮች ከማብራሪያው ጥሩ ግንዛቤ እንደጨበጣችሁ እየተማመንን በቀጣይ በዚሁ የስራ ክፍል ጥናት የተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ የቀረቡ ሀተታዎችን ይዘን የምንቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ቸር ቆዩን!

Federal government attorney Fb page

Exit mobile version