Site icon ETHIO12.COM

ምርጫ ደርሷልና በራችሁን ብቻ ሳይሆን ልባችሁንም ክፈቱ!


ነጻ አስተያየት በበላይ ባይሳ  – ጽሁፉ የጸሃፊው ብቻ አስተያየት ነው 

በስህተትም፣ በድፍረትም፣ ባለማወቅም ሆነ ሆን-ብሎ ጥፋት ያጠፋም ማንኛውም አካል ራሱን ይመልከት። ለበደለኛነቱም ይፀፀት። ላለፈ ክረምት ግን ቤት አይሰራም እና ቀሪ ረጅም የጋራ መንገድ በተሻለ ሁኔታ ለመጓዝ ይቅር መባባሉ የቅድመ ምርጫው አካል ቢሆን የተሻለ ይሆናል። አዋጩ መንገድም እሱ ይመስለኛል። በመሰረቱ ህግ ውሳኔ ይሰጣል እንጂ አያስታርቅም። ይቅርታ ደግሞ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ነው። መንግስትም ጉልበታም መሆኑን አሳይቷል።

ፖርቲዎች ለመመረጥ መንግስት ሲሆኑ የሚከውኗቸውን ተግባራት በጠራና ግልፅ በሆነ መንገድ ያለአድልኦ እና ያለተፅዕኖ ለህዝቡ ለማቅረብ ያላቸው ዝግጁነት የምርጫው ወሳኝ መቅድም ነው።ፖርቲዎች በፓለቲካ ኘሮግራሞቻቸው የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎች፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ስራ አጥነት ቅነሳ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ግሽበት፣ የንግድና የታክስ ስርአት፣ የሰው ሃብት ልማት ስራዎች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የፍይናንስ ስርዓት፣ የልማት ፖሊሲዎች፣ ጠንካራ ሃገርና ትውልድ መገንቢያ መንገዶች፣ ስነ-ህዝብ፣ ስነ-ፆታ፣ ሙስናን የመታገያ ስልቶች፣ የህግ የበላይነት እና የፍትህ ስርዓት፣ የመሬት ፖሊሲ፣ ቴክኖሎጂ እና ግሎባላይዜሽን፣ የግብርና ፖሊሲ፣ የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ ባህልን ከመጠበቀና ከማሳደግ አንፃር፣ ብዝሃነትን ማስተናገድ፣ የድህረ-ዘመናዊነት ተፅእኖ መቋቋም እና ወዘት… ጉዳዮች በፖርቲያቸው መነፅር ምን መምሰል እንደሚገባ የሚዳሰስበት እና አማራጭ አተያዮች የሚቀርብበት ነው ተብሎ ይታመናል።ይሁንና በባለፉ ምርጫዎች ይህ አይነት የፖለቲካ ይዘት እምብዛም በተደራጀ እና በሰነድ ደረጃ አልተስተዋለም። ይልቁንም በአብዛኛው በመድረክ ላይ መዘራጠጥና አንዱ ሌላኛውን በማሳነስ ራሱን ብቻ በማግነን ግለሰባዊ ገፅታ-ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ፤ አንዱ ሌላውን በማሸማቀቅና በመክሰስ፤ በምርጫ ቅስቀሳ ስም አንዱ የሌለኛውን ሀጢያት በማብዛት ህዝቡን በተስፋ ወደፊት ከመውሰድ ይልቅ የሙሾና እንጉርጉሮ ይዘት ያለው ምንም የማይፈይድ እንዴት እንደተጎዳ እንጂ እንዴት እንደሚድን መፍትሄ የማያመላክት ወደኋላ ጎታች የምርጫ ቅስቀሳ ባህል ነው የገነባነው። .ከላይ የተገለፁት እና የተለያዩ ምክንያቶች እንዲሁም የመንግስት እጅግ ዘለግ ያለ ጣልቃ-ገብነትና እጅ ማርዘም ተዳምረው የአፍሪካ ብሎም የሃገራችን ምርጫ የተጓዘበት መንገድ እጅግ የማይመችና ፒስታ የበዛበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምርጫ በመጣ ቁጥር ለሰላማዊ ዜጎች ስጋትና አስጨናቂ የምጥ ጊዜ እንዲሁም የግጭት ጥንስስ ሆኖ ሞት ደግሞ ግቡ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አህጉራችንም ሆነች ሃገራችን ውድ ዋጋ እየከፈለች እዚህ ደርሳለች።

ከመንግስት አካላት “እኔ ነኝ የማሸንፈው” የሚል የቅድመ ትንበያ የድምዳሜ ነጠላ ዜማ ተቀባይነት የለውም። ከወዲሁ የተዓማኒነት ጥያቄ ያስነሳልና ከዚህ መሰል መዳፈር መቆጠብ ያሻል። ህዝብም ሊከበር ይገባል። ምክንያቱም ውጤት የሚገለፀው በምርጫ አስፈፃሚው አካል ድምፅ ከተቆጠረ በኋላ በሚሰጥ መረጃ ብቻ መሆን ይኖርበታልና።

የሃገራችን የፖለቲካ ታሪክ የነበረበትን ፖርቲ አፍርሶ ሌላ የሱቅ በደረቴ ፖርቲ ለሟቋቋም ሲሯሯጥ፤ የሊቀመንበርነቱን ቦታ በይገባኛል ክስ ሲጦዙ፤ እንትን የሚባል የእገሌ ፖርቲ ነው እንትን ደግሞ የእነእገሊት ሲባባሉ፤ የፖርቲውን ገንዘብ መዝብሮ ለራሱ እንትን ገዛ ብለው ሲጓተቱና ሲካሰሱ፤ የፖርቲ ማህተምና ሎጎ በማሳተም የተጠመዱ አለፍ ሲልም አንዱ በሌለኛው ላይ ሲዶልት እና ህዝብ ሲያስቅበትና ሲሳለቅበት የነበረ የምርጫ ታሪክ ነው ያለፈው።ታድያ የፖለቲካ ድርጅቶች መቼ ለህዝቡ ተጨነቁና? መቼ ስለ ትልልቅ ሃገራዊ አጀንዳዎች እና ለሃገር ስለሚበጁ ጉዳዮች ለማሰብ ጊዜ አገኙና? ቢያገኙስ አቅሙ ይኖር ይሆን? ያው መስራት እንደ መናገር ቀላል ስላይደለ ማለቴ ነው።አንዳንዱ ፖርቲዎች የስማቸው መለያየት ካልሆነ በስተቀረ ማኒፌስቶዋቸው ሳይቀር አንዳይነት ወይም አንዱ ከሌላው እንዳለ ገልብጦ (copy-pest) በሰነድነት ይዘው እንደነበሩ ልብ ይለዋል። ይታያችሁ ሃሳቡ ሀገር ለመምራት ነው እኮ። ይህ አክሳሪ፣ አሳሪና አሰልቺ የነበረው አካሄድ ግን አንድ ቦታ ላይ ሊቆምና ሊያበቃ ግድ ይላል።

ከዚህ አንፃር የዘንድሮ ምርጫ የተለየ ገፅታ ይዞ የመጣ ይመስላል። ለዚህም መሳካት እንደ ጅምር የሚወሰደው የምርጫ ቦርድ ወቅታዊ ቁመና፣ የህዝቡና የመንግስት ፍላጎት እንዲሁም የፍርድ ቤቶች ዝግጁነት በዚሁ ከዘለቀ ይበል የሚያሰኝ እና ለምርጫው ሂደት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ ይችላል።በነገራችን ላይ በምርጫ ቦርድ ላይ ለተደረገው የሪፎርም ስራ ይበል የሚያሰኝና የሚመሰገን ብቻ ሳይሆን እየተሰራ ያለው የሰከነ አሰራር እና የአመራር ብቃት ለሌሎችም ተቋማት መልካም መነሻ እንደሚሆን በወፍ በረር ማድነቅ ይገባል።

የፖለቲካ ፖርቲዎች እና አክቲቪስቶች እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት እና የሚድያ ተቋማት ድሮ ከለመዱት የተፋዘዘ እና የውገና አካሄድ ውስጥ ወጥተው ቅቡልነት ወዳለበት የምርጫ ሂደትና አሳማኝ የሆነ ውጤት ተመዝግቦ ሃገሪቷ መዳህ የጀመረችውን የዲሞክራሲ ጅምር ወደ ወፌ-ቆመች እንዲያድግ ተገቢ ሚናቸውን በመጫወት እና ሃላፊነታቸውን በመወጣት ታሪካዊ አሻራቸውን ማኖር ይጠበቅባቸዋል።ህዝቡም በስሜት ሳይሆን በስሌትና ከሃገራዊ ጥቅም አንፃር ከተፅዕኖ እና ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ተላቆ የተሻለ አማራጭ፣ አዋጭ እና ገዢ ሃሳብ ይዞ የመጣውን ብቻ መምረጥ ይኖርበታል። ውጤትንም በፀጋ የመቀበል ባህልን ለማዳበር በሁሉም አካላት ልምምድ ማድረግም ግድ ይሆናል።መንግስትም በየደረጃው አስፈላጊውን የቅድመ ሁኔታ ስራ መስራትና ሂደቱም በአብዛኛው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሚናውን መጫወት ብቻ ሳይሆን ግልፅነት እንዲኖረው ያገባኛል እታዘባለሁ ለሚል ባለድርሻ አካላት ሁሉ የመጫወቻ ሜዳውን ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን በሩንና ልቡን መክፈት ይኖርበታል።

የዘንድሮ ምርጫ ከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የተለየ ስለመሆኑም ከሂደቱ እና ከውጤቱ በኋላ በገለልተኞች ማረጋገጫ ማግኘት ሲችልነው የመንግስት ቁርጠኝነትም የሚለካው። የባለፉትንም ምርጫዎች የበለጠ ማነፃፀር የሚቻለው። ስለዚህ የመንግስ ሚና ድርብርብ ይሆናል ማለት ነው።በአንፃሩ ደግሞ ምርጫው እጅግ ከባድ እና በፍርሃት ቆፈን የተጠፈረ ሊሆን እንደሚችልም ከወዲሁ መገመት ተገቢ ይሆናል። በተለይም ከመንግስት አካላት “እኔ ነኝ የማሸንፈው” የሚል የቅድመ ትንበያ የድምዳሜ ነጠላ ዜማ ተቀባይነት የለውም። ከወዲሁ የተዓማኒነት ጥያቄ ያስነሳልና ከዚህ መሰል መዳፈር መቆጠብ ያሻል። ህዝብም ሊከበር ይገባል። ምክንያቱም ውጤት የሚገለፀው በምርጫ አስፈፃሚው አካል ድምፅ ከተቆጠረ በኋላ በሚሰጥ መረጃ ብቻ መሆን ይኖርበታልና።

በህግ ጥላ ስር ያሉትን ቁጥሩ የማይናቅ ድጋፍና ተከታይ ያላቸውን በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ጥረት ቢደረግ የምርጫው ድምቀት ከመሆኑም ባሻገር ለተፈጠረው ውጥረት እንደማርገቢያ ሆኖ ሊረዳ ይችላል። በፓለቲካ ይህ አይነቱ አካሄድ የዘመናዊ ፓለቲካ ባህልና አካሄድ ብቻ ሳይሆን ለድርድር እንደበር ማስከፈቻ ቁልፍ ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል።በስህተትም፣ በድፍረትም፣ ባለማወቅም ሆነ ሆን-ብሎ ጥፋት ያጠፋም ማንኛውም አካል ራሱን ይመልከት። ለበደለኛነቱም ይፀፀት። ላለፈ ክረምት ግን ቤት አይሰራም እና ቀሪ ረጅም የጋራ መንገድ በተሻለ ሁኔታ ለመጓዝ ይቅር መባባሉ የቅድመ ምርጫው አካል ቢሆን የተሻለ ይሆናል። አዋጩ መንገድም እሱ ይመስለኛል።በመሰረቱ ህግ ውሳኔ ይሰጣል እንጂ አያስታርቅም።

ይቅርታ ደግሞ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ነው። መንግስትም ጉልበታም መሆኑን አሳይቷል።ማንም ሰው ከህግ በታች መሆኑም ትምህርት ተወስዶበታል እና ሃገሪቱን ወደፊት ለማስቀጠል እንዲቻል ለምጣዱ ተብሎ … እንደሚባለው ሁሉ መንግስት አሁንም ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ሆደ-ሰፊ ሆኖ ከሰማይ በታች ሊያደርግ የሚገባውን አሟጦ መጠቀም ይጠበቅበታል።ሁሉም በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ-ምርጫ ሃላፊነቱን በሚገባ ከተወጣ እንዲሁ በደፈናው በእንትና ላይ ተሞርኩዤ፤ በእከሌ ላይ ተንጠላጠጥዬ ነው እንዲህ የሆንኩት የሚሉ ውሃ የማይቋጥር ተልካሻ ምክንያቶች፣ ተረት-ተረት እና አርተፊሻል ትወናና አካሄድ ቦታ አይኖራቸውም።ሲጠቃለል ከልብ ካለቀሱ… እንደሚባለው ሁሉ ለዘንድሮ ምርጫ ፍትሃዊነት፣ ተዓማኒነት፣ በአብዛኛው ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በተለይ ደግሞ ሃገሪቱ ከተለማመደችው አዙሪት ውስጥ መውጣት እንድትጀምርና ህዝቡ በመረጠው ብቻ እንዲተዳደር ምርጫ ቦርድና መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በራችሁን ብቻ ሳይሆን ልባችሁንም ክፈቱ!በላይ ባይሳጥር 29/2013 ዓ.ም

Exit mobile version