Site icon ETHIO12.COM

በማይካድራ ከተማ ከ17.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ

በንፁኃን ግድያ የተጠረጠሩ ‹‹እኛ ሰላማዊ ዜጎች ነን›› አሉ

ጥቅምት 30 እና ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በማይካድራ ከተማ በደረሰ ጉዳት ከ17.6 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ፡፡

ይኼ የተገለጸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በከተማው በተጠቀሱት ቀናት በንፁኃን ነዋሪዎች ላይ ዘርን መሠረት ባደረገ ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በማለት ተጠርጥረው የታሰሩ 36 ተጠርጣሪዎችን፣ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት፣ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ የሠራውን የምርመራ ሪፖርት ለፍርድ ቤት ሲያቀረብ ነው፡፡ 

ቡድኑ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣ በከተማው የደረሰውን የንብረት ጉዳት የሚያሳይ ፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ተናግሯል፡፡ ቡድኑ የ20 ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከጎንደር ሪፈራልና ከሳንጃ ሆስፒታሎች የ177 ሰዎችን የጉዳት መጠን የሚገልጽ ማስረጃዎች ማሰባሰቡንም አክሏል፡፡

ተጨማሪ የሰው ምስክሮች ቃል መቀበል፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የ117 ጅምላ መቃብር የወጣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት መቀበልና ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማስረጃዎች ማሰባሰብ እንዲችል ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ 

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ሪፖርት ቀደም ብሎ ካቀረበው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የምርመራ ሒደቱን የሚያሳየው ሰነድ (ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን) ኮፒ ምርመራው ምን ላይ እንደደረሰ ለመከታተል እንዲረዳቸው ኮፒ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ የሚደረገው አንድ ሰው የፈጸመው የወንጀል ተሳትፎ ተለይቶ ሲታወቅ መሆኑን ጠቁመው፣ በማይካድራ በንፁኃን ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ (ፖሊስ እንደሚለው) ተሳትፋችኋል ብሎ እየመረመራቸው በመሆኑ፣ ተሳትፏቸውን ለይቶ ማቅረብ እንዳለበት፣ ይህ ካልሆነ ግን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፈቀድ እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው ጥቅምት 30 እና ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በመሆኑ ሦስት ወራት ከ18 ቀናት እንደሆነው ጠበቆቹ አስታውሰው፣ መርማሪ ቡድኑ በሦስት ወራት ውስጥ የተጠርጣሪዎችን ተሳትፎ ለይቶ እንዲያቀርብ ማድረግ ካልተቻለ፣ መርማሪ ቡድኑ የጅምላ ምርመራ ውጤትን ማቅረብ እንደ አማራጭ እየተጠቀመበት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁጥር 59(2) ድንጋጌ ላይ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ገደብ ባይቀመጥም፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የሕጓ አካል ባደረገቻቸው ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎችና አፍሪካ ሰብዓዊ መብት ቻርተር መሠረት መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በጣም ውስብስብና በርካታ አካላት ተሳትፈውበት የሚፈጸመውን የሽብር ወንጀል ለመከላከል ወጥቶ ሲሠራበት የነበረው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 እንኳን ከአራት ጊዜ በላይ ጊዜ ቀጠሮ እንደማይሰጥም አስታውሰዋል፡፡ በ108 ቀናት ውስጥ የተጠርጣሪዎችን ተሳትፎ ለይቶ ማቅረብ ካልተቻለ ገና በርካታ 14 ቀናቶች እንደሚቀሩም አክለዋል፡፡

በምርመራ መዝገቡና በጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ሰነድ ላይ የሚኖረው የምርመራ ይዘት ተመሳሳይ ነው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ጠበቆቹ፣ በምርመራ መዝገቦች ላይ የሚጠቀሱት ከባባድ ድርጊቶች የዋስትና መብት ለማስከልከል ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ከሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር በመቀናጀት የተፈጸመ ወንጀል ነው፤›› በማለት እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ መገንዘብ እንደሚችለው በችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች በዚያ ደረጃ የሚሆኑ እንዳልሆኑ ግንዛቤ መውሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹን ማግኘት እንዳልቻሉና በታሰሩበት ቦታ ሄደው እንደሚያገኟቸው ሲጠይቁ፣ መርማሪው ወደ ሌላ ኃላፊ፣ ኃላፊው ደግሞ ወደ ኮሚሽነሩ በማለት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከአሥረኛው ቀን እንዳገኟቸው በማስረዳት፣ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች እንደነገሯቸው (ለጠበቆቹ) እነሱ የፈጸሙት ግድያ እንደሌለና ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን ነው፡፡ 

በወቅቱ የእርስ በርስ ግጭት ስለነበር ሁሉም በየፊናው ተበታትኖ እንደነበርና ስለሆነው ነገር ምንም እንደማያውቁም እንደነገሯቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ በደረሰው ጉዳት ተጎጂዎች በስሜት ተነሳስተው ጉዳት ሊያደርሱባቸው እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ፖሊስ በአንድ ማቆያ ቦታ እንዳስቀመጣቸው ገልጸው፣ የተወሰነ ጊዜ እዚያው (ማይካድራ) አቆይተው ወደ ጎንደር እንደወሰዷቸውና ከዚያም ወደ አዲስ አበባ አምጥተው እንዳሰሯቸው አስረድተዋል፡፡

እነሱ (ተጠርጣሪዎቹ) ከምንም ውስጥ እንደሌሉበትና እንዲያውም በእነሱ ላይ በተለይ በማይካድራና በጎንደር በቆዩባቸው ጊዜያቶች ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው፣ በረሃብና ሕክምና ዕጦት ሦስት አብረዋቸው የታሰሩ ሰዎች እንደሞቱ ተናግረዋል፡፡ የዩኒሴፍ ሐኪሞች ለማከም ቢጠይቋቸው መከልከላቸውን ከመካከላቸው በጥይት የተመቱ እንዳሉና በክላሽ ሰደፍ ጨምሮ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ተናግረዋል፡፡ 

ወደ አዲስ አበባ አባ ሳሙኤል እስር ቤት ከተዛወሩ በኋላም ሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን እያገኙ እንዳልሆነና እስር ቤቱ የሚጠበቀው በማረሚያ ቤት ፖሊሶቸ በመሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸው ሊጠይቋቸው ሲመጡ ሊያስገቧቸው እንዳልቻሉና ‹‹የሉም›› ብለው እንደሚመልሷቸው አስረድተዋል፡፡ አብረዋቸው በእስር ቤት የሚገኙ ሕፃናት ልጆቻቸው (ሰባት ናቸው) ተጠርጣሪ ስላልሆኑ ሕክምና መከልከላቸውንም አክለዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው እነሱን ከማይካድራ ለማፈናቀልና ንብረቶቻቸውንና ቤታቸውን ለመውሰድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች በታሰሩበት ቦታ የሰጡት ቃል በምስክርነት ፎርም ላይ መሆኑንና ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ለምስክርነት ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት ጥበቃ አድርገው ሊለቋቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ የማይካድራው ጭፍጨፋ የተፈጸመው ቀድሞ የነበረው ኃይል ሲለቅና አዲስ የሚገባው ኃይል ሲገባ የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለባቸውም አክለዋል፡፡ 

እንደ ጠበቆቹ ገለጻ ሕፃናቱ የሥነ ልቦና ችግር እንደገጠማቸውና ሕገ መንግሥቱ፣ የአፍሪካ ሕፃናት መብቶች ቻርተር፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ታልፈው መታሰራቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርመራው በሕግ አግባብ እየተካሄደ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረው፣ የተጠየቀው 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ እንዲደረግና የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡  

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ ባቀረበው መከራከሪያ እንደገለጸው፣ በሌላ ቦታ ስለደረሰባቸው ነገር እሱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሮ፣ ቡድኑ የሚያውቃቸው ከጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ወንጀሉ በተደራጀና በቡድን የተለያዩ ስለቶችን በመጠቀምና መታወቂያ በመጠየቅ በማንነት ላይ ያነጣጠረና የተፈጸመ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወንጀሉ በጋራ የተፈጸመ በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹን የለዩዋቸው ተጎጂዎች መሆናቸውንና በማቆያ ከነበሩ 4,000 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረቡት ወንጀሉን በቀጥታ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ የ22 ተጠርጣሪዎች የተከሳሽነት ቃል መቀበሉንና በምስክርነት የተቀበላቸው እንደሌሉ አክሏል፡፡  

በጎንደር ሆስፒታል ኮማ ውስጥ ያሉ እንዳሉና እስከሚነቁ እየተጠበቁ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ የሞቱትን ሰዎች በሚመለከት በቁጥር እንዳልገለጸና በ117 ጉድጓዶች የተቀበሩት ሰዎች አስከሬን ምርመራ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን ጠቁሞ፣ የጠየቀው 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ለተጨማሪ ምርመራ 11 ቀናት ፈቅዷል፡፡ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ፣ ቤተቦቻቸው እንዲጠየቋቸው እንዲያደርግ፣ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን መብት ባከበረ መልኩ እንዲይዛቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ለየካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ Byታምሩጽጌreporter amharic

Exit mobile version