Site icon ETHIO12.COM

በጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለመሰማራት 134 ባለሀብቶች የቦታ ጥያቄ አቀረቡ

በጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 134 ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገለጸ።

የገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክት አካል በሆነችው የጎርጎራ ከተማ የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ነገ እንደሚከናወን የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳዳር አስታውቋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የፌደራል ፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙ ይጠበቃል ፡፡

ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት መታቀፏ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህበድ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 134 የሚደርሱ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶቹ እያንዳንዳቸው እስከ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት የኢንቨስትመንት የጥናት ፕሮጀክት በማዘጋጀት ለአስተዳደሩ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጎርጎራና አካባቢው ደረጃውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ሎጆች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋና ወተት እንዲሁም ማር ማቀናበርና የተፈጥሮ ማዕድን ልማት ምቹ መሆኑን አስረድተዋል።

ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም በዘርፉ መሰማራት ለሚሹ ባለሀብቶችም ከ300 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት ቦታ በጥናት በመለየት በቅርቡ ለማስረከብ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስተዳደሪው ገልጸዋል፡፡

የጎርጎራና አካባቢው ህዝብ ነገ በሚከናወነው የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ- ሥርዓት የሚታደሙ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉንም ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

በጣና ሐይቅ ዳርቻ የተመሰረተችው ጎርጎራ ከጎንደር ከተማ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በርካታ ጥንታዊ ገዳማትና ታሪካዊ ስፍራዎች ያሉባት ቀደምት የቱሪስት መዳረሻ ናት፡፡

ጎርጎራ በ16ኛ ክፍለ ዘመን አጼ ሱስንዮስ የገነቡት ቤተ-መንግስት በቅርብ ርቀት የሚገኝባት ታሪካዊ ከተማ መሆኗም ተመልክቷል፡፡. Via ENA

Exit mobile version