በአማራ ክልል በአንድ ፕሮጀክት ብቻ በደረሰ ውድመት ከ3 ሺህ በላይ ሠራተኞች ተበተኑ

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት የኢንቨስትመንት ዘርፉ መቀዛቀዝ አሳይቷል፡፡

ይኹን እንጅ በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ በተፈጠረው ሰላም ዘርፉ መነቃቃት ማሳየቱን አንስተዋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ464 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ እና ከ98 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ 4 ሺህ 724 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ኀላፊው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ464 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የኀይል፣ የግብዓት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት ተችሏል፤ በዚህም 324 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 255 ፕሮጀክቶች ምርት አቁመው የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህም ከ63 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት 98 ኢንዱስትሪዎችን በክልሉ በማቋቋም ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል፡፡ ከ38 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ሚና ተጫዎተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአበባ ልማት 128 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው አቶ እንድሪስ የገለጹት፡፡

በበጀት ዓመቱ በታየው ሰላም የኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃት ቢያሳይም አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በዘርፉ ላይ ጉዳት መድረሱን ነው ቢሮ ኃላፊው ያስገነዘቡት፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች ውስጥ ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም አበባ ልማትን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ጉዳቱም ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚኾን ነው ኀላፊው የገለጹት፡፡ በቋሚነት ይሠሩ የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ ሠራተኞችም ተበትነዋል፡፡ አንድ ሠራተኛ በአማካይ 4 ቤተሰብ ቢኖረው እንኳ ከ12 ሺህ በላይ ቤተሰብ ችግር ላይ ወደቀ እንደማለት ነው፡፡ በቀጣይ በክልሉ የደረሰውን የጉዳት መጠን ቢሮው ይፋ እንደሚያደርግ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማኅበረሰቡ የሥራ እድልና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ሚናቸው የጎላ በመኾኑ ማኅበረሰቡ እንደራሱ ሀብት የመጠበቅ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

See also  ብልጽግና አክራሪነትና በፖለቲካ ገበያ ትርፍ ለማግኘት በሚተጉ ላይ የጋራ አቋም መያዙን አስታወቀ

አሚኮ

Leave a Reply