Site icon ETHIO12.COM

የትህነግ ታሳሪዎች – ከበረሃ ከተማረኩ ጀምሮ ሰብአዊ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንን፣ ሲያዙ ተኩስና ማስፈራራት እንደነበር ገለጹ

“ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባሰራጨው ጽሁፍ እንዳለው ከትግራይ ተማርከው ወደ አዲስ አበባ የመጡትንና በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙትን የቀድሞ የትህነግ አመራሮችና አክቲቭ ባለስልጣናት ካሉበት ዘንድ በመሄድ አነጋግሯል። ኮሚሽኑ በስም የዘረዘራቸውን በጥቅል ተቅሶ “የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል” ሲሉ ምስክርነት መስጥታቸውን አመልክቷል።

ከመቀለ ሲሸሹና ወደ በረሃ ሲያመሩ ተኩስ መኖሩን አስታውቀዋል። ስለ አያያዛቸውና ስላሉበት የእስር ቤት የራሱን ትዝብት በበጎ ጎኑ ያስቀመጠው ኮሚሽኑ የፍርድ ሂደታቸው ተጠናቆ በዋስ የሚፈቱ ካሉ በዛው አግባብ እንዲታይላቸው አሳስቧል።

ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙሉ መግለጫውን እንደሚከተለው ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሀም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረ መድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል። እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል። ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

Exit mobile version