Site icon ETHIO12.COM

የጫካ ትግሉን የሚመሩት ጌታቸው አሰፋ በጠና መታመማቸው ተሰማ

የቀድሞ የአገር ውስጥ ደህነትና ዋና ሃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ በጠና መታመማቸው ተሰማ። በካናዳ የትህነግ አመራር የቅርብ ሰው ለኢትዮ 12 እንደነገሩት ከፍተኛ መዋቅሩ መታመማቸውን ከሰማ ሰንባብቷል።

ለውጡን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ህግ ስለሚፈልጋቸው የትግራይ ክልል አስተዳደር አሳልፎ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ቢቀርብለትም ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል። አቶ ጌታቸው ይመሩት የነበረውን ተቋም መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ይዘው ወደ ትግራይ ከሄዱ በሁዋላ ይህንኑ መዋቅር በመጠቀም አገሪቱ ውስጥ በተላያዩ ደረጃዎች ትርምስ ሲፈጥሩበት እንደነበር መንግስት በቁጥጥር ስር ካዋላቸው አካላት መረዳቱን በተደጋጋሚ መጥቀሱ አይዘነጋም።

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በሁዋላ በትህነግ ስራ አስፈሳሚ ውስጥ የገቡትና ከሁሉም በላይ ሃይል እንደገነቡ የሚነገርላቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ትህነግ ከመቀሌ ሸሽቶ ሲወጣ ዋናውን ሃይል ይዘው ወደ በረሃ አምርተዋል።” የትግራይ የመከላከያ አዛዥ” የሚባሉት የቀድሞ ጀነራል ወረደ፣ በንግድ ስራ ተሰማርተው ከነበሩት ጀነራል ጻድቃን ጋር በመሆን ዋናውን ሃይል ይዘው የመሸጉት አቶ ጌታቸው አሁን ላይ በጠና መታመማቸው ከመገለጹ ውጭ የህመማቸውን ዓይነት እንደማያውቅ ዜናውን ያደረሰን የካናዳው የመረጃ ምንጭ ጠቁሟል።

አቶ ጌታቸው የእነ አቶ መለስ እድሜ ክልል የሚገኙና የስልሳዎቹን እድሜ የዘለሉ መሆናቸው ይታወቃል። አቶ ጌታቸው በምስል ሳይታወቁ ብዙ መቆየታቸው እንደ ልዩ ሰው ያስቆጠራቸው ” ገንዘብ ሲደመር ጭካኔ ስለላ ” የሚል መርህ ያላቸው መሆኑንና ሚዲያ ልዩ ጀግና ያደረጋቸው ሰው እንደሆኑ የሚያውቋቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

በአሜሪካ የትህነግ አመራሮች ቅርብ የሆኑ ምንጮች ጋር ለማረጋገጥ ብንሞክርም ለጊዜው የሰሙት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ቢሆንም የሚያስገርም እንዳልሆነ አመልክተዋል።


Exit mobile version