Site icon ETHIO12.COM

ዕድሜዋ 4 ዓመት የማይሞላትን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ተከሳሽ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 4 ዓመት የማይሞላትን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ተከሳሽ በህፃኗ ላይ የክብረ ንፅህና መገርሰስ ባያደርስም በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አሸናፊ ከድር ሰኢድ የተባለው ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀፅ 627/1 ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሰኔ 20/2012 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው “ ፈለገ ህይወት ትምህርት ቤት ” አካባቢ በሚገኘው የተከሳሽ መኖርያ ቤት ውስጥ 4 ዓመት የማይሞላትን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈራት በመሆኑ በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል ።

ዐቃቤ ህግም የህፃኗን ቤተሰቦችን አናግሬ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ህፃኗ ድርጊቱ በተፈፀመበት ዕለት ለቤተሰቦቿ ብትናገርም ቤተሰቦቿ የህፃኗ ገላ ላይ ምልክት ያላዩ በመሆኑ ወዲያውኑ አጣጥበው ጉዳዩን ህግ እንዲያውቀው ከማድረግ ይልቅ ጉዳት አልደረሰባትም በማለት ሳያመለክቱ የቀሩ ቢሆንም ህፃኗ ግን እንቅለፍ በምትተኛበት ወቅትና በቀን ጭምር ስነ ልቦናዋ በመጎዳቱ ከተለመደው ባህሪዋ ወጣ ያለ የቅዠት ምልክት በተደጋጋሚ ማሳየቷን በማየታቸውና በጎረቤቶቻቸው ግፊት የመጡ መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል ።

በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የሰው እና ከጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የህፃኗን የጉዳት መጠን የሚገልፅ የሕክምና የምስክር ወረቀት በሰነድ ማስረጃነት አቅርቧል።

በሰነድ ማስረጃነት የቀረበው የሕክምና የምስክር ወረቀት ላይ በክብረ ንፅህና መገለጫ አካሏላይ መገረስስ ባያሳይም በሠበር መዝገብ ቁጥር 107166 የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የግብረ ስጋ ግንኙነት ድፍረት ተደርጎ የክብረ ንፅህና መገረስስ ባይኖርም ግንኙነት አልተፈፀመም ማለት የማይቻል መሆኑን አስገዳጅ ውሳኔ በሰጠው መሰረት የፌደራሉ የመጀመር ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል ሲል ተከሳሽ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል ።

ወላጆች እንደዚህ አይነት ድርጊት በልጆቻቸው ላይ ሲፈፀም ወንጀሉን አልተፈፀመም በሚል በቸልተኝነት ከማለፍ ይልቅ ለፍትህ አካላት በማሳወቅ ጉዳዩን ህግ እንዲይዘው ማድረግ ተገቢ ነው።

Exit mobile version