Site icon ETHIO12.COM

የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።

የአማራን ሕዝብ እረፍት መንሳት ቋሚ አጀንዳቸዉ ያደረጉ ኃይሎች መቸም ቢሆን ይተኙልናል ብለን አንጠብቅም። የአማራ ሕዝብ ቋሚ እረፍት የሚያገኘዉ በቋሚነት እረፍት ሊነሱት ቆርጠዉ የተነሱትን ኃይሎች በሕግ አግባብ አደብ ከያዙ ብቻ ነዉ። እነዚህ ወገኖች በዚህ ልክ አደብ እስኪገዙ ድረስ ግን የአማራን ሕዝብ ለስዓትም ቢሆን እረፍት እንደማይሰጡት እናዉቃለን።

የዛሬዉ በአጣየና አካባቢዉ የተከሰተዉ ጉዳይም የዚሁ የአማራን ሕዝብ እረፍት የመንሳት ያደረ አጀንዳ ቅጥያ ነዉ። የአጣየዉ ጥቃት የአማራን ሕዝብ በቋሚነት እረፍት መንሳት አጀንዳቸዉ ያደረጉ ኃይሎች ቅንጅታዊ የሥራ ዉጤት ስለመሆኑ ብልጽግና በደንብ ይገነዘባል።

ስለዚህ እነዚህ የአማራን ሕዝብ በቋሚ ጠላትነት ፈርጀዉ እየሠሩ ያሉ ኃይሎች በኢትዮጵያ ምድር ህልዉና/አቅም እስካገኙ ድረስ የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሁሌም ስጋት ዉስጥ ለማስገባት መንቀሳቀሳቸዉ አይቀርምና፤ የአማራ ሕዝብ ከመቸዉም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮና የተደቀነበትን ስጋት እስከወዲያኛዉ ለማስወገድ በአንድ ልብ እንዲንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም የክልሉ መንግሥት የድርጊቱን አፈጻጸም ከስሩ በማጣራት መወሰድ ያለበትን ሕጋዊ እርምጃ በመዉሰድ ሰለድርጊቱ አስፈላጊዉን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።

የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት

Exit mobile version