Site icon ETHIO12.COM

የፊታችን አርብ የጠ/ ሚ ዐብይ አህመድ 3ኛ ዓመት በዓለ ሲመትን በማስመልከት የድጋፍ ሰልፍ ሊካሄድ ነው



የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ 3ኛ ዓመት በዓለ ሲመትን አስመልክቶ በተሸከርካሪ የታጀበ የድጋፍ ሰልፍ የፊታችን አርብ በአዲስ አባበ ሊካሄድ ነው፡፡

ከማህበረሰቡ የተወጣጡ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ባለሃብቶች የድጋፍ ሰልፉን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አርብ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 3ኛ ዓመት በዓለ ሲመትን አስመልክቶ በተሽከርካሪ ትርኢት የታጀበ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ለሀገር ሰላም መስራት እንደሚያሸልምና እንደሚያሥክብር ወጣቱ ትውልድ የሚረዳበት ይሆናልም ተብሏል፡፡

በሰልፉ አስተባባሪነት ከወጣቶች የተወከለው ሞቲ ሞረዳ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገራቸውና ለሌሎች ሰላም በመስራታቸው ከዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዳገኙ ሁሉ ኢትዮጵያዊንም ልናወድሳቸው ይገባል ብሏል፡፡

በተሸከርካሪ ታጅቦ የሚካሄደው ትርዒትም መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያን ትናንት የነበራቸው አንድነት፣ ሰላምና አብሮነት እንዲጠናከር ያግዛል ተብሏል።

በመግለጫው ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉ የሃይማኖት አባቶችም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና አንድነት የሚሰራ ሁሉ እውቅና እና ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ይህንን በማድርግ ትልቅ ስራ የሰሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መደገፍና ማመስገን ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ መልአከ ህይወት አባ ሃይለ ገብርኤል ነጋሽ እንዳሉት ዓለም የሰላም ሰው ያላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማመስገን እና እውቅና መስጠት ተገቢ ነው።

መልካም ያደረገን ማመስገን የሃይማኖት አንዱ መገለጫ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላምና እርቅ ዘረፍ ሃላፊ ሼህ መሀመድ ሲራጅ ኡመር እንዳሉትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘመናት ተራርቀው የነበሩትን የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ማቀራረባቸው ታሪክ የማይረሳው ድንቅ ስራ ነው።

በዚሁ ተግባራቸው ዓለም እውቅና የሰጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሁላችንም ልናመሰግናቸውና እውቅና ልንሰጣቸው ይግባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሃፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በሰጡት አስተያየትም ስለሀገር ሰላም ይመለከታኛል በሚል ሊካሄድ ታሰበው መርሃ ግብር ትክክለኛ ሃሳብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ስለ ሰላም የሰራን ማመስገንና ለሰላም ዘብ መቆም የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባዋልም ብለዋል።

ከሀገር ሽማግሌና ባለሃብት የተወከሉት አቶ ቶፊቅ ከድር እንዳሉትም በዕለቱ ሁሉም ስለ ሰላም የሚያወራበትና ስለ ሰላም ዘብ መቆሙን ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል፡፡

አርብ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በተሸከርካሪ ታጅቦ የሚካሄደው ትርዒት “የሀገሬ ሰላም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወን ይሆናል።. (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version