Site icon ETHIO12.COM

የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች በከተማም ሆነ በዙሪያው ተንቀሳቅሶ ለመስራት መቸገራቸውን ተናገሩ

በሽፍታነት የተሰማሩ ግለሰቦች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠሩብን ነው ሲሉ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

በሽፍታነት የተሰማሩ ግለሰቦች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠሩባቸው መሆኑን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከህዝቡ ጋር በጋራ ጠንክሮ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ሽፍቶች በየጊዜው የግፍ ግድያና እንግልት በህዝቡ ላይ እየፈጸሙ በመሆኑ በሰላም መውጣትና መግባት አልቻሉም ።

በከተማም ሆነ በዙሪያው ተንቀሳቅሶ ለመስራት መቸገራቸውንም ገልጸዋል።

የከተማው አስተዳደር ህዝቡን የሰላም ጥያቄ አልመለሰም፣ ከቻግኒ ግልገል በለስ መንገድ ደህንነት ጥበቃ ይደረግለት የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።

በአካባቢው ኮማንድ ፖስት ከህዝቡ ጋር በጋራ መስራት አለበት፣ ሽፍቶችም መያዝና ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል ሲሉ ጠይቀዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ እንዳሉት በየጊዜው በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ ለሰው አዕምሮ የሚከብድ ተግባር ነው።

በቀጣናው የተደቀነው ፈተና ከባድ ቢሆንም በጋራ ተናቦ መስራትና ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ተገቢ ነው ብለዋል።

የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማቆም ለሌላ ርሃብ መጋለጥ በመሆኑ ሁሉም ወደ ስራው እንዲመለስም መክረዋል።

በተመሳሳይ የክልሉ ጸጥታና ደህነነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በበኩላቸው ከህሊና በላይ የሆነው የንጹሃን ግድያ ሁሉንም ያሳዘነና እንቅልፍ የነሳ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።

ከፍተኛ የኮማንድ ፖስቱ አመራር ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ቶሊና በበኩላቸው በተወሳሰበ ችግር ላይ ችግር በመደራረብ መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ከስሜት በመውጣት እለታዊ ስራውን ማከናወንና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴው መመለስ እንዳለበት መክረዋል።

ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከህዝቡ ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎችም ማህበረሰቡን በማረጋጋት የንግድ እንቅስቃሴውን ለማስጀመር የቤት ስራ ወስደው ተመካክረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።. Via (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version