ETHIO12.COM

“3000 ሌሊቶች” Andwalem Arage

ከ1997 ዓ.ም.የቅንጅት መሪዎች “ፓርላማ እንግባ፣አንግባ” ክርክር ፣ እስከ በእስር ቤት ውስጥ ይቅርታ ጠይቀን እንውጣ፣ አንውጣ ክርክር ፣ እንዲሁም እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የግፍ ፅዋ በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ እንዴት ሞልቶ እንደፈሰሰ የምትተርከዋ “3000 ሌሊቶች” የተሰኘችው አዲሷ መጽሐፌ በጥቂት ቀናት ውስጥ በአሜሪካ ታትማ ለአንባቢዎች ትደርሳለች።

መጽሐፏ ምንም እንኳን የእስር ቤት ማስታወሻ ብትሆንም የእኔን የግል ታሪክ ብቻ የምትተርክ ሳትሆን፣ ወደ 13 አመታት ያህል የሚሆነውን ያሳለፍነውን የኢትዮጵያን የፓለቲካ ትግል ታሪክ በወፍ በረር የምትዳስስ፣ በእስር ቤት ውስጥ አብረውኝ የነበሩ የተወሰኑ በሕይወት የሌሉና ያሉ የቅንጅት መሪዎችንና እንዲሁም የጥቂት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ታሪክ በአጭር በአጭሩ ከእነ ፎቶግራፋአቸው ተካቷል።

ከ2004 ዓ.ም.እስከ 2010ዓ.ም. በዘለቀው የእስር ወቅትም አብረውኝ ከነበሩ እስረኞች የተወሰኑ ጓድኞቼ ታሪክ ተካቷል። በተለይም ከአሰቃቂው የቃሊቲ እስር ለማምለጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ያጡ ደባሎቼ ታሪክና እነርሱን ያፈራውን ሁኔታ ትዳስሳለች። ባሎቻቸው በታሰሩበት ወቅት በሚያስደምም ፅናት ከባሎቻቸው ጎን የቆሙ ያልተዘመረላቸው ስድስት ጀግና ሚስቶች ታሪክ ከእነፎቶግራፋቸው ተካቷል። ሌሎችም አያሌ አነጋጋሪና መፍትሄ የሚሹ ታሪኮችን ያካተተች ዳጎስ ያለች ጥራዝ
በፈጣሪ እርዳታ በጥሩ ሁኔት ተዘጋጅታ ቀርባለች።

“3000 ሌሊቶች” አራተኛ መጽሐፌ ስትሆን ከሦስቱ በተለይ የመጀመሪያ ሁለቱ እስር ቤት እያለሁ የታተሙ በመሆናቸው በጓድኞቼ ድካም ለአንባቢ የደረሱ ናቸው ።” በዘመናት መካከል” የተሰኘችው ሦስተኛ መጽሐፌም ብትሆን በአብዛኛው የቀደሙ ሥራወቼ ስብስብ በመሆናቸው የ”3000 ሌሊቶች”ን ያህል አልደከምኩባቸውም። በጣም በብዙ ዐይን ገላጭ መረጃዎች የተሞላች መጽሐፍ በመሆኗ ሌሎች ወገኖችም ለተመሳሳይ ሥራዎቻቸው በማጣቀሻነት ሊጠቀሙባት ይችላሉ።

Exit mobile version