ETHIO12.COM

ተደራጅተው ከባድ የዘረፋ ወንጀል ይፈፅሙ የነበሩ 34 ተጠርጠሪዎች እና 12 ተሸከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጥናት ላይ ተመርኩዞ ባደረገው ቁጥጥር ተደራጅተው ከባድ የዘረፋ ወንጀል ይፈፅሙ የነበሩ 34 ተጠርጠሪዎች እና 12 ተሸከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቀ፡፡

መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ም/ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ከባድ የዘረፋ ወንጀል ይፈፅሙ እንደነበረ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ የወንጀል አፈፃፀም ሁኔታ እጅግ አደገኛ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው ሃሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ የሚያዘጋጁ፣ የጥበቃ ሰራተኛ መስለው ለሚቀጠሩ ወንጀል ፈፃሚዎች ሃሰተኛ ተያዥ የሚያፈላልጉና በሚዘረፈው ተቋም ላይ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ እንዲቀጠር አድርገው ሌሎች የጥበቃ ሰራተኞችን በተለያዩ አደገኛ መድሃኒቶች በማደንዘዝ ለዘረፋ ምቹ ሁኔታን በሚፈጥሩ ግለሰቦች የተደራጀ የዘረፋ ቡድን እንደነበረ አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተዘረፈውን ንብረት ጭኖ የሚወስድ፣ ደልሎ የሚያሻሽጥ፣ ለተሰረቁ ተሸከርካሪዎች የሻኒሲ ቁጥራቸውን የሚቀይር እና ንብረቶቹን የሚገዛ ቡድን ያለበት አደገኛ ስብስብ እንደነበር ም/ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡

በግለሰቦቹ አደገኛ ወንጀል አፈፃፀም የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በንፋስ ስልከ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የአንድ ግለሰብ ህይወት በተጠርጣሪዎቹ ማለፉን ም/ኮሚሽነር ሃሰን ገልፀዋል፡፡ተጠርጣሪዎቹ የምርመራ መዝገባቸው ተጠናቆ ለሚመለከተው የፍትህ አካል የሚላክ መሆኑን አብራርተው ፖሊስ ባደረገው እልህ አስጨራሽ የሌት ተቀን ክትትል 12 ተሸከርካሪዎችን የሻንሲ ቁጥር የሚቀየርበት ማሽንና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለመቆጣጠር ባደረገው ብርቱ ክትትል የምርመራና የክትትል አባላት የሚያስመሰግን ተግባር መፈፀማቸን ገልፀው ለውጤቱ ስኬታማነት ህብረተሰቡ ላደረገው ተባባሪነት ም/ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ via Addis Ababa administration

Exit mobile version