Site icon ETHIO12.COM

ሩሲያ የቀጠናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች


👉 የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራም ገለጸች



ኢትዮጵያ የራሷን እና የቀጠናውን ደህንነት ለመጠበቅ በምታደረገው ጥረት የሩሲያ መንግስት ድጋፉ እንደማይለያት የሩሲያ አምባሳደር ያቭጋኒ ተርክን አስታወቁ። ሀገራቸው የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣የሩሲያ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ደህንነትን ለማጠናከር በተለያየ መንገድ ድጋፍ እያደረገ ነው።

የቀጠናውን ደህንነት በተሻለ መልኩ ማጠናከር የሚቻለው ፖሊቲካዊ መፍትሄዎችን በማጠናከር እንደሆነ ያመለከቱት አምባሳደሩ ፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያና ሩስያ ለበርካታ ዓመታት በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል ።

በተለይ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በነበረችበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራታቸውን ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ደህንነት እና ፀጥታ በዋናነት ማስጠበቅ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ፤ ይህንን መቀበል አለብን ያሉት አምባሳደሩ ፤ለዚህም ሩሲያ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል ለማጠናከር ሰፊ እርዳታዎችን ሰጥታለች ብለዋል ።

ማንኛውም ሀገር የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ከሁሉም ቅድሚያ የኢኮኖሚ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት የጠቆሙት አምባሳደሩ ፣ በዚህም የሀገራችው መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ሩሲያ የቀጠናውን ደህንነት ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ሁለንተናዊ መልክ እንዳለውም አመልክተዋል። በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ እያደረጉት ያለው ጥረት የሶስቱ ሃገራት ጉዳይ ቢሆንም ፤ የሀገራቱን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍ አስታውቀዋል ።

“ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ግዙፍ ሀገር ናት፤ የቀጠናው ሀገራት የደህንነት ጉዳዮች የሚወስኑት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው”ያሉት አምባሳደሩ ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና ደህንነት የሚሰፍን ከሆነ የቀጠናው ሰላም እና ደህንነትም የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል።

ሀገራቸው የኔውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር በጋራእንደምትሰራ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ተጠቃሚ ሃገሮች አባል ከሆነች እኛ ለመርዳት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እኤአ 2019 በሩሲያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደው በአፍሪካ-ሩሲያ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት በኒውክሌር መስክ መሰረታዊ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

የሁለቱ ሃገራት ወቅታዊ የኔውክሌየር የትብብር ስምምነት በዚህ ዓመት ታህሳስ ላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ የኒውክሌር ሃይልን ለልማት መጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት ካፀደቀ በኋላ ተግባራዊ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘርፉ ተጨማሪ አዳዲስ የመግባቢያ ሰነዶችን ለመፈራረም መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ስምምነቶቹ የኒውክሌር ሃይል አጠቃቀም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚረዱ በአቅም ግንባታ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኒውክሌር ትብብር በሃይል ማመንጫ ብቻ የሚወሰን እና በአጋጣሚ የሚደረግ አለመሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ ፣ የኒውክሌየር የሀይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ውስብስብ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፤ ጊዜ፣ ጥረትና ገንዘብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

የተለመደው የኒውክሌር ጣቢያ ግንባታ የጊዜ ገደብ ወደ አስር ዓመት የሚጠጋ ነው። ግንባታው እስኪከናወን ሌሎች ተያያዥ እቅዶችን ወደ ተግባር በመለወጥ ጠጠቃሜ መሆን ይቻላል ብለዋል።

የሃይል ማመንጫ ጣቢያው ከመጠናቀቁ በፊት በሕክምና ዘርፍ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ቢተገበር ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። “በተጨማሪ በየዓመቱ ከሚሰበሰበው የሰብል ምርት ሃያ አምስት ከመቶ በበሽታዎች እና በተለያዩ ምክንያቶች ይባክናል ይህንን ለመቀነስና በሌሎችም ኢንዱስትሪዎች ላይ የኒውክሌር ሀይል ልማት ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ የቴክኖሎጂ ትብብሮች በሌሎችን የቴክኖሎጂዎች በማበልጸግ ዘርፎችም በጋራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አምባሳደሩ ጠቁመዋል።. (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version