ሩሲያና ኢትዮጵያ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ


ሩሲያና ኢትዮጵያ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች መስኮች የሚያደርጉትን ሁሉን አቀፍ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ከሆኑት ኢያቭገኒ ተርኪን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አገልግሎቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መረጃ አስታውቋል።

በዚህ ወቅት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሁለቱ ሀገራት የረጅም አመት የታሪክና የባህል ትስስር ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ወቅታዊ የኢትዮጵያን ፈተና ለማሻገር እገዛ በሚያደርጉ መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፕሮፌሽናል ተቋም ለመገንባት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ትብብር አቅም እንደሚፈጥርለት የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በችግር ወቅትም ተፈትኖ ፍሬያማ ስኬት የታየበት በመሆኑ በቀጣይም በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ትብብሩ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ጉዳይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ስታደርግ የነበረው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በተለይ ሀገራቱ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች ትብብራቸው ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአቅም ግንባታ መስክና በመረጃ ልውውጥ የተጠናከረ የጋራ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ገንቢ ውይይት ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ጋር ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

ሩሲያ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ካላቸው አምስት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በሚነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ ከሌሎች አጋር ሀገራት ጋር ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ሀገሪቱ የውስጥ ችግሮችን በራሷ መፍታት የምትችል ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን በጸጥታው ምክር ቤትና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች እያንጸባረቀች ትገኛለች ሲል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: