Site icon ETHIO12.COM

የኦሮሚያ ክልል 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አስታወቀ ። ምርጫው ህዝቡ በነፃነት ድምፁን የሚያሰጥበት በመሆኑ ከቀደሙት ምርጫዎች ልዩ እንደሚያደርገው ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞኪራሲያዊነቱን ለማረጋገጥ ከላይ እስከ ታች መዋቅር ተዘርግቶ በትኩረት እየተሰራ ነው። በዚህ ሂደት እስከ አሁን በተደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳ በክልሉ ያገጠመ የጎላ ችግር የለም ።

ምርጫ ቦርድ በአስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንደ መንግሥት አስፈላጊውን ኃላፊነት በመወጣት፣ እንደ ተወዳዳሪም የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል። ችግሮች ሲያጋጥሙም በውይይት ለመፍታት ከክልል እስከ ወረዳ መዋቅር ተዘርግቷል ፣ችግሮች በጋራ የሚፈቱበት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት እንደመንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ እየሠራ ነው፣ ከዚህ በተቃራኒ ያሉ አካሄዶች በየትኛውም መልኩ በፓርቲያቸውና በመንግስታቸው ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የኮቪድ ፕሮቶኮሎች ሳይጓደሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባወጡት መመሪያ መሰረት በክልሉ የምረጡኝ ቅስቀሳ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በኮቪድ ምክንያት ምርጫውን ችግር ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል ።0

ከክልሉ ሰላም አንፃር የምርጫው ሰላማዊነት ማረጋጋጥ ትልቁ የክልሉ መንግሥት ትኩረት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ፣ ህዝቡ ለመመዝገብም ሆነ በነፃነት የፈለገውን ለመምረጥ የሚገድብው ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል ።

በምዕራብ ኦሮሚያ በተወሰኑ ወረዳዎች ህገወጥ እንቅስቃሴ መኖራቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ አካባቢውን ሰላማዊ በማድረግ ህዝቡ ያለምንም ስጋት ድምጹን ሰጥቶ እንዲገባ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።

በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ያለውን አስተዋፅዎ በመገንዘብ የበኩላቸውን አስተዋፅዎ እያበረከቱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከዚህ በላይ በተሳካ መልኩ አብሮ ለመስራት በቅርቡ የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።

በክልላችን 178 የምርጫ ክልል አለ፣ በሁሉም ምርጫ ክልል ሁሉም አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሟልተዋል እስከ አሁን ድረስ ከአቅማችን በላይ የሆነ ችግር የለም። እስከ አሁን በተደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳ የህዝብ ተሳትፎ በህዝብ ዘንድ ጥሩ ስሜትና ዝግጅቶች ይታያሉ ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎን በተመለከተ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በምርጫ የፖለቲካ ስትራቴጅያቸውን ለህዝብ በማሳወቅ ወደ ስልጣን መምጣት የሚፈልጉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምረጡኝ ቅስቀሳ ሂደት ያልገቡ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተቃራኒውም በምርጫ መሳተፍ ፍላጎት የሌላቸው የፅንፈኝነት መንገድን የመረጡ በፅንፈኝነት መንገዳቸው ምርጫ መካሄድ የለበትም በማለት ሁል ጊዜ በምክንያት ምርጫውን ለማደናቀፍ ህዝብን ወደማይፈለግ አቅጣጫ መግፋት የሚፈልጉ አካላት አሉ ። እነዚህ ሀይሎች በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም፣ ህዝቡም ይህንን እያወገዘ ለምርጫው ራሱን እያዘጋጀ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ባለው አቅም ሁሉ እየሰራ ይገኛል፣ ለወደፊትም ይሰራል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ህዝቡና ፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዎ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን

Exit mobile version