Site icon ETHIO12.COM

በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የክልሉን ሰላምና ገፅታ በሚገነባ መልኩ ሰላማዊ ምርጫ እንደሚያካሂዱ ገለጹ

በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የክልሉን ሰላምና ገፅታን በሚገነባ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ:: በክልሉ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተጠቆመ::

የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ በደል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለ27 ዓመታት በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የነበረ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው ለውጡን ተከትሎ በተገኘው ውጤት ሶማሌ ክልል ሰላም የሰፈነበት ክልል ሆኗል፣ ይህንን እድል በመጠቀም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየሰሩ ነው::

እንደ መንግሥትም ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የገጠሙ ተግዳሮቶች በየደረጃው እየፈታን ነው ብለዋል::

ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቱ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መስፋፋት፣ ወሰን አካባቢ በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃቅን ግጭቶች መኖርና በፅንፈኝነት አስተሳሰብ የተቃኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅታዊ ተግዳሮቶች ቢሆኑም ይህንን በመቋቋም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በክልሉ በሚገኙ 93ቱ ወረዳዎችና በስድስቱም ከተሞች ምርጫ ቦርድ በአስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያለምንም እንቅፋት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል::

እንደ አቶ አሊ ገለፃ ፤ ኮቪድ -19 ወረርሽኝ በተመለከተ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደ መንግሥት ተወስዷል፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባወጡት መመሪያ መሰረት የኮቪድ ፕሮቶኮሎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ነው:: ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በትራንስፖርት፣ በግብይት ስፍራዎች፣ በምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅት አፍንጫ እና አፍ መሸፈኛ እንዲያደርጉ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራበት ነው። ሆቴል አካባቢ በሚደረጉ ሁነቶችም በሕጉ መሰረት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው::

በአጠቃላይ በክልሉ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የማይካሄድበት ቦታ የለም ያሉት አቶ አሊ የምረጡኝ ቅስቀሳ በክልሉ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ኃይሎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ፖለቲካ አጀንዳቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በጋራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው፤ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ባላድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል:: (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version