Site icon ETHIO12.COM

“ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመተባበር እንዲሁም ሰከን ብሎ በመምከር ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ በደም ፍላት መፍታት አንችልም ”

ከተባበርን የማንወጣው መከራ፤ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም – አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር

የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ሲካሄዱ የዋሉ ህዝባዊ ሰልፎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ፡፡

የክልሉ መነግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ማምሻውን በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡ ሲሆን በዛሬው እለት በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልድያ፣ ሀይቅ፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ላይ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰልፉ ዓላማም በተለያየ ጊዜና ቦታ የአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም መንግሥትን የሚጠይቅ ሲሆን በተለይም ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና አካባቢው በጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ኃይል የተከፈለውን የህይወት መስዋእትነትና የደረሰውን ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ምክንያት በማድረግ የተጠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሰልፉ ላይ የተገኘው ህዝብ ሀዘኑን በምሬት የገለጸ መሆኑንም አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ በመሆኑ ለአስተባባሪዎችና ለተሳታፊው ህዝብ ያላቸውን አክብሮትና ምስጋናም በክልሉ መንግሥት ስም ገልጸዋል፡፡

ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ዋና ዳይሬክተሩ የአማራ ህዝቦች ችግር በሰልፍ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን በመረዳት ወጣቱና መላው ህዝብ ለዘለቄታዊ መፍትሔዎች ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የአማራ ህዝብ ጠላቶች ለረዥም ዓመታት መጠነ ሰፊ ሴራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩበት ሁኔታ ግዘፍ ነስቶ በገቢር የተገለጸበት ዘመን በመሆኑ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመተባበር እንዲሁም ሰከን ብሎ በመምከር ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ በደም ፍላት መፍታት አንችልም ብለዋል፡፡

ለረዥም ጊዜ ሲሰራ የቆየው አማራን የማዳከም ስትራቴጂ መሬት የነካ መሆኑን ጠላቶቻችን በተደጋጋሚ እየነገሩን ይገኛሉ ያሉት አቶ ግዛቸው በአሁኑ ሰዓት አማራ ክልልን በሁሉም አቅጣጫ በመክበብና በመወጠር ሀገር የመበተን ግቡን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ኃይል ያለ መሆኑን ሰልፈኛው ህዝብም ሆነ አስተባባሪዎች ሊረዱ አንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በሰልፉ ላይ የተላለፉት መልእክቶች በአብዛኛው ጥሩ አንደነበሩም ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወሱ ሲሆን አንዳንድ የግለሰቦችን ሰብእና የሚነኩ መልእክቶች አንድነታችን ከመሸርሸር ውጭ አስተማሪ እንደማይሆኑ ተናግረዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ያለን አንደመሆናችንም ዴሞክራሲን መለማመድ ሲገባን የፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮችንና አንዳንድ ከሰልፉ ዓላማ ውጭ የሆኑ መልእክቶችን ይዞ ኢዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን እንካሂዳለን እያልን ኢዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን ልናበረታታ አይገባም ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአጣየና አካባቢውን አሁናዊ ሁኔታ ያብራሩት አቶ ግዛቸው የሸዋሮቢት ከተማ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ወደ ከተማው ተመልሶ በመግባት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ያለ መሆኑን አስታውሰው የአጣየ ከተማ ላይ የደረሰው ውድመት ግን ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪዎች ተመልሰው የሚያርፉበት መጠለያቸው በመውደሙ ምክንያት የመንግሥትን ድጋፍ ወደሚያገኙባቸው አጎራባች ከተሞች በጊዜያዊ መጠለያ ላይ የሚገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አካባቢው በአሁኑ ሰዓት ወደ መረጋጋት የተመለሰ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግዛቸው እነዚህ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሰላም ናቸው የምንለው ግን በእነዚህ አካባቢዎች ተከባብሮ በሚኖረው ማኅብረሰብ መካከል ሰርጎ በመግባት ተተኳሽና የቡድን መሳሪያዎችን ታጥቆ ከተማ ያወደመውና ህዝብን የጨፈጨፈው ኃይል ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ግዛቸው በአካባቢው የተቋቋመውን ኮማንድ ፖስት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን የሠጡ ሲሆን ኮማንድ ፖስቱ የክልሉ አመራርም የሚሳተፍበትና በጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት በመሆኑ በሂደት የሚገጥሙ ጉድለቶችን በጋራ እያረምን ችግሩን በዘላቂነት የምንፈታበት እድል ሰፊ ነው ሲሉ ተናረዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ከተባበርን የማንወጣው መከራ፤ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም ያሉ ሲሆን የትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች ይሁኑ መላው ህዝባችን የአማራን ህዝብ ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር የአማራን ህዝብ ሞት እና አንግልት ለማስቆም በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ አንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 12/2013 ዓ.ም (አማራ ኮሙኒኬሽን)

Exit mobile version