Site icon ETHIO12.COM

የመራጮች ምዝገባ ቀነ ገደብ እንደሚራዘም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነገ እንደሚጠናቀቅ ቀነ ገደብ የተቀመጠለት የመራጮች ምዝገባ እንደሚራዘም አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የመራጮች ምዝገባ ሂደትን የተመለከተ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ የክልል ርዕሳነ መስተዳደርች የየክልላቸውን የመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህም በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች የመራጮች ምዝገባ 80 እና ከ80 በመቶ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገባቸውን ነው ያስታወቁት።

በቀሪ ጊዜያት አፈጻጸሙን በታቀደው አግባብ ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የደቡብ፣ የአማራና የሀረሪ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ክልሎቹ ምዝገባው በተጀመረበት ሣምንት አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ በተሰሩ የግንዛቤ ተግባራት መሻሻሎች መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በቀሪ ጊዜያት አፈጻጻሙን ለማሻሻል እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

በጋምቤላ ክልል የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ በመጀመሩ ምክንያት እስካሁን ያለው አፈጻጸም 41 በመቶ መሆኑም ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ አፈጻጻም 43 በመቶ ሲሆን፤ በአፋር ክልል ከ453 ሺህ በላይ ሰዎች የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸው ተገልጿል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው በክልሎች ያለው የመራጮች ምዝገባ አፈጻጻም ወጥነት ያለው ባለመሆኑ የምዝገባ ቀነ ገደቡ እንደሚራዘም አስታውቀዋል።

ለምን ያህል ጊዜ ይራዘም የሚለው ግን በቦርዱ ቀጣይ ስብሰባ እንደሚወሰን ነው የገለጹት።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ ክልሎች በቀጣይ ቀናት የመራጮችን ምዝገባው በስፋት እንዲከናወን በቁርጠኝነት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴራል መንግስት ግብዓቶችን በአውሮፕላንና በሄሊኮፕተር ከማጓጓዝ ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የምርጫውን ሂደት በሚመለከት ከክልል ርዕሳነ መሰተዳድሮች ጋር የሚያደርጉት ውይይት ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመላክቷል።

Exit mobile version