Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔ ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች

እ.ኤ.አ በ2022 የሚካሄደውን ሁለተኛውን የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ፎረም ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭን ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል። ውይይታቸው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2022 የሚካሄደውን ሁለተኛውን የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው ከሩሲያ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ለክቡር አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ገልጸውላቸዋል።

አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ስለጽ/ቤታቸው ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የአፍሪካና ሩሲያ ኩባንያዎች በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል የኢኮኖሚ ትብብር ማህበር መቋቋሙን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመጪው ክረምት ከአፍሪካ ህብረትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ሩሲያ ይህንን መድረክ ለመፍጠር የወሰደችውን ተነሳሽነት አድንቀው ሁለተኛውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት አቶ ደመቀ ገልጸውላቸዋል።በሁለቱ አገራት መካከል በደህንነት፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በጤና እና በስነ-ምድር ምርምር ዘርፎች ያላቸውን ትብብር በተመለከተ ምክክር አድርገዋል።

አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሩስያ ጉብኝት እንዲያደርጉ የሩስያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ የላኩትን ግብዣ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው


Exit mobile version