Site icon ETHIO12.COM

የቀይ ሽብር አዋጅ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው መመሪያ

አብርሃም ተወልደ

 የዛሬው ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተከሰቱ አያሌ ምሁራንና ወጣቶች ቀርጥፎ የበላው “ቀይ ሽብር” አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው “የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መመሪያ” ይፋ የተደረገበት ዕለት ነበር።ቀኑ ሚያዝያ 12 / 1968 ዓ.ም ነበር ።ወታደራዊ መንግስት “ደርግ” የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መመሪያ አድርጎ ያወጀበት ቀን፡፡

ከቻይና አብዮት የተኮረጀው ይህ ቀመር በሶስተኛው ዓለም የሶሻሊስት ለውጥን ለማምጣት ፍቱን ነው ተብሎ የታመነበት ሲሆን፤ መሰረታዊ ይዘቱም “በወዝአደሩ፣ በአርሶአደሩና በተራማጅ ንዑስ ከበርቴ አብዮታዊ ጥምረት የሰፊው ህዝብ ጠላቶች ተብለው የተለዩትን “ፊውዳሊዝምን” “ኢምፔሪያሊዝምንና” “ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን” መደምሰስ ነው፡፡

ይህ ዓላማም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመስከረም ወር 1980 እውን ሆነ።ለተመለከተውና ነገሩን ላጤነው ሁሉ እውር ድንብሩን “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ብሎ ሰኔ 1966 የተነሳውን ደርግ እዚህ ጣራ ላይ ለመድረስ ምን ያህል አስደናቂ ረጅም ጉዞ እንደተጓዘ ግልጽ ነው፡፡

የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ከታወጀበት በኋላ ቀጣዩ ርምጃ የፕሮግራሙ አስፈጻሚ አካል የሆነውን ጊዜያዊ የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ማደራጀት ሆነ።የአዋጁ መታወጅ እና የጽህፈት ቤቱ መቋቋም ወቅቱ “አበይት ተግባር ሰፊውን ህዝብ ማንቃት እና ማደራጀት ነው” እያሉ ይወተውቱት ለነበሩት እንደ “መኢሶን” ላሉ የግራ ክንፍ ሀይሎች ትልቅ ድል ነበር።

ጽህፈት ቤቱን እንዲመራ የተሰየመው አስራ አምስት አባላት ባሉት ኮሚሲዮን የሊቀ መንበርነቱን ስፍራ ከመያዝ አንስቶ ግልጽ የሆነ የበላይነት የነበረው “መኢሶን” የጽህፈት ቤቱን መዋቅር ድርጅታዊ አቅሙን ለማፈርጠም ተጠቀመበት።ጽህፈት ቤቱ በተቋቋመ በጥቂት ወራት ውስጥ የድርጅት ቁሳዊ ሆነ ሰብአዊ ኃይል ቀላል የማይባል እመርታ አሳየ፡፡

በተጓዳኝም ከተሞችን ለመቆጣጠር ቁልፍ የሆነውን “የከተማ ልማት እና ቤት ሚኒስቴር” በመቆጣጠሩ እና በ1968 መጨረሻ ላይ በተደረገው የቀበሌ ምርጫ ደጋፊዎቹን ለማስመረጥ በመቻሉ ትልቅ የመደላደል ስሜት ተሰማው።ስለሆነም የመንግስት ስልጣን ወደ ሰፊው ህዝብ ተወካዮች የሚተላለፈው እንደ “ኢሕአፓ” በሐሳብ ግትርነት ደርግን በመጋፈጥ ሳይሆን ደርግ የፈጠረው መዋቅር በዘዴ በመጠቀም ነው ብሎ ቢያስብ እምብዛም አይገርምም፡፡

ይሁን አንጂ ደርግ “የመኢሶንን” ስሌት ሳይረዳው ይቀራል ብሎ ማሰብ የፖለቲካ የዋህነት ነበር።ደርግ ሌላው ሁሉ ነገር ቢቀር በፖለቲካ ስልጣን ጉዳይ ቆቅ መሆኑን ከአንዴም ሁለቴ አሳይቷል።በዚያ ላይ ደግሞ የሁለት አመት የአብዮት ትምህርት ቤት “የግራ ክንፉን ማርክሲስታዊ” ዘይቤን ድርጅቱ እንዲጨብጥ አስችሎታል።ስለዚህም ነገሩ “ብልጥ ለብልጥ” ሆነና የጉልበት ፍተሻውን አይቀሬ አደረገው።አይቀሬ እየሆነ የመጣው ድራማም በአብዛኛው በ1969 ዓ.ም መጀመሪያ ተጀምሮ በዓመቱ ማብቂያ ላይ ተጠናቀቀ፡፡

የደርግ እና የኢሕአፓ ክረት

በመጀመሪያ ደርግ ለዘብተኛ የሆነውን የግራ ክንፍ አጋር በማድረግ የእድገት እመርታው ባስደነገጠው እና ማዕቀብ የሌለው ተቃውሞ ባበገነው “በኢሕአፓ” ላይ ዘመተ።በዚህ ረገድ አያሌ የሰራተኛውና የብዙሃን ድርጅቶች የ“ኢሕአፓ”ን መፈክር አንግበው ሰልፍ የወጡበት የ1968ቱ “ሜይ ዴይ” በዓል ወሳኝ ወቅት ነበር።በዚያን ወቅት ደርግና የግራ ክንፍ አጋሮቹ ኢሕአፓ እስካለ ድረስ እነሱ መኖር እንደማይችሉ በቅጡ ተረዱ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ሁለቱ ባላንጣዎች ሰይፋቸውን መሳል ጀመሩ።በክረምቱ ወራት የታየው አንጻራዊ ዝምታም ዶፍ ያዘለ ዳመና ነበር፡፡

ሰው ሰራሽ የሆነው የሽብር ክረምቱ ጅማሮ

የተፈጥሮ ክረምት ሲያባራ ሰው ሰራሹ የሽብር ክረምት መስከረም ላይ ጀምሮ ዓመቱን ሙሉ ቀጠለ።ደርግ የኢሕአፓ ታጋዮችንና ደጋፊዎችን በመግደል ኢሕአፓ በደርግ አቀንቃኞችና ባለሟሎች ላይ የሽምቅ ጦርነት በማወጅ ፉክክር ተያያዙ።ከሁለቱም ወገን ታሪኩን ለመጻፍ (እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ግድያውን ማን ጀመረው ብሎ መጠየቅ) መሳሪያቸውን ስለው ከተፋጠጡ ሁለቱ ባላንጣ ሰራዊቶች መካከል የመጀመሪያውን ተኩስ ማን ከፈተ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው።በዚህም ሆነ በዚያ ፍልሚያው አይቀሬ እየሆነ መጥቷል።አንዴ ከተጀመረ ወዲያም እያሻቀበ እንጂ እየለዘበ አልሄደም፡፡

የመገዳደሉ አበይት ምዕራፎች ከሞላ ጎደል ይህን ይመስሉ ነበር።መስከረም 13 ኢሕአፓ እንደ ቀንደኛ ጠላት ያየው የነበረው በደርጉ አንደኛ ምክትል ሊቀ መንበር በሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም ላይ የግድያ ሙከራ አድርጎ ሳይሳካላት ቀረ።እንዲያውም ከሙከራው ያመለጠው የመንግስቱ ቡድን በአንድ በኩል ለራሱ ተወዳጅነት ለማትረፍ በሌላ ወገን ደግሞ “የኢሕአፓን” ክስረት ለማሳየት ተጠቀመበት፡፡

በዚያው ወር ውስጥ “ኢሕአፓ” “የመኢሶን” አመራር አባል እና የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ባልደረባ የነበረውን ዶክተር ፍቅሬ መርዕድን ሰንጋ ተራ መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ ሚስቱን በመጠበቅ ላይ ሳለ አድፍጦ በመግደል የመጀመሪው አብይ ሰላባ አገኘ።በድርጊቱ በጣም የተበሳጨውም ደርግ “አንድ አብዮታዊ ህይወት በሺህ ፀረ ህዝቦች ህይወት ይመነዘራል” የሚል መግለጫ ካወጣ በኋላ የኢሕአፓ አባሎችንና ደጋፊዎችን በገፍ በማሰርና ከታሰሩትም መካከል መርጦ በመረሸን የበቀል ርምጃውን ወሰደ፡፡

ደርግ በአባላቱ ላይ የወሰደው “አብዮታዊ ርምጃ”

የመንግስት የማጥቃት ርምጃ አፍቃሬ “ኢሕአፓ” ተብለው በተፈረጁት የደርግ አባላት ላይ ጥር 26 ቀን 1969 “አብዮታዊ ርምጃ” ከተወሰደባቸው በኋላ ተጠናክሮ ቀጠለ።በተለይ በሚቀጥሉት ወራት አከታትሎ በወሰዳቸው ሁለት አሰሳዎች በህቡዕ ገብተው የነበሩትን አንዳንድ “የኢህአፓ አባላት” መሪዎችን በተለይ ቀንደኛ አባላቱን ከመግደሉና ከማሰሩ ባሻገር ሲቪሉን ትጥቅ በማስፈታት መቅኔውን ሰለበው።

እነዚህ “የአሰሳና ድምሰሳ” ርምጃዎች “በቀይ ሽብር” ስም በኋላ ለታወጀው ዘግናኝ የታሪክ ምዕራፍ መቅድም መሆናቸው ነው።“ቀይ ሸብር” በዋነኛነት ያነጣጠረው “በኢሕአፓ” ላይ ሲሆን፤ ቀስ በቀስ ግን “የኤርትራ ህዝባዊ አርነት ግንባር እና ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ” ብሎም ከደርግ ጎራ ያፈነገጠው “መኢሶን” ሳይቀር የሽብሩ ዒላማ ሆኑ፡፡

ሌሎች የግራ ክንፍ ቡድኖች ኢሕአፓን በክፉ አይን እንዲመለከቱት ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ ተሸቀዳድሞ ራሱን “የላብ አደሩ ፓርቲ ነኝ” ብሎ በማወጁ ነው።የሁሉም አላማ በወቅቱ ገንኖ የነበረው “ማርክሲስታዊ ሌኒናዊ” አስተሳሰብ የሌኒን ጽንሰ ሀሳብ ማዕከል የነበረውን ግንባር ቀደም “የሰራተኛው መደብ ፓርቲ” ሆኖ ለመገኘት ነበር፡፡

በሰራተኛው ማህበራት እና በህዝባውያን ድርጅቶች የኢሕአፓን ያህል ሰርገው ለመግባት ያልቀናቸው እነዚህ ቡድኖች ኢሕአፓን “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ብለው አጣጣሉት።በእነሱ ስሌት የፖለቲካ ፓርቲ ባህል ባይተዋር በሆነባት ኢትዮጵያ የወዝ አደሩ ግንባር ቀደም ፓርቲን ተጣድፎ ማወጅ ወይ ድንቁርናን ወይ ስግብግብነትን አመላካች ነበር።ስለዚህም ይመስላል በኋላ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረትን (ኢማሌድኀ) ከፈጠሩት ከእነዚህ ፀረ ኢሕአፓ ከነበሩት የግራ ክንፍ ቡድኖች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ራሱን ፓርቲ ብሎ ያልሰየመው።

ከስማቸው እንደምንረዳው የመረጡት ስያሜ “ንቅናቄ” ፣ “ሊግ” ፣ “ትግል” ፣ “ድርጅት” ወይም “ሰደድ” ነበር።ሐቀኛ ግንባር ቀደም ፓርቲ ሊመሰረት የሚችለው ሰፊው ህዝብንና ተራማጅ ኃይሎችን ያለመታከት በማንቃት እና በማደራጀት ነው ብለው በአጽንኦት ተከራከሩ።ኢማሌድኀን በየካቲት 1969 ያቋቋሙት ወደዚህ የመጨረሻ ግብ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመድረስ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013


Exit mobile version