ኃይሌ ፊዳና እና የግሌ ትዝታ

ሊነበብ የሚገባው መፅሐፍ ‹‹ኃይሌ ፊዳና እና የግሌ ትዝታ››

(እ.ብ.ይ.)

በምዕራባውያኑ የአብዮት ታሪክ ዋነኛው ተጠቃሽና ለጀርመን፣ ለጣሊያንና ለአውስትራሊያ አብዮት መነሻና አቀጣጣይ የሆነው፤ እንዲሁም ለአውሮፓውያኑ የመጀመሪያ አብዮት ተደርጎ የሚጠቀሰው በ18ኛው ክ/ዘ መጨረሻ አካባቢ የፈነዳው የፈረንሳይ አብዮት ነው፡፡ የፈረንሳይ አብዮት የባሪያ ንግድን ለማስቆምም የመጀመሪያው ነበር፡፡ ፈረንሳይ ባርነትን ባዋጅ ካስወገደች ከ50 ዓመት በኋላ ነው እንግሊዝ ሃሳቡን ለፓርላማዋ ያቀረበችው፡፡

በሐገራችንም በ1966 ዓ.ም የፈነዳው አብዮት የንጉሱን ስርዓት ገርስሶ ጥሏል፡፡ አብዮቱ በመምጣቱ የተደሰቱ ብዙ ዜጎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን በአብዮቱ ማግስት የተከናወነው የጥሎ-ማለፍ የፖለቲካ ጨዋታ ሐገሪቷን አኬልዳማ አድርጓታል፡፡ በለውጡ ተስፋ አድርገው የነበሩ ብዙ ዜጎች በልጆቻቸው የእርስበርስ እልቂት ተስፋቸው ከንቱ ሆኗል፡፡ አብዮቱ የገዛ ልጆቹን እንክት አድርጎ በልቷል፡፡ በጊዜው የነበሩ ከሞት ያመለጡ ወይም የተረፉ አብዮተኞች ዕድሜ ሠጥቷቸው በሚፅፏቸው ታሪኮች ዘመናቸው ብዙ ያልተበረበረ ሚስጥርና ግፍ የተሞላው እንደነበረ በየጊዜው ይገልፁልናል፡፡ ያለፈውን ማወቅና መመርመር ያሁኑን ለመዋጀት ይጠቅማልና በአጠቃላይ የታሪክ ፀሐፊዎቹን እናመሰግናለን፡፡

በዶክተር አማረ ተግባሩም የተፃፈው ‹‹ኃይሌ ፊዳና እና የግሌ ትዝታ›› መፅሐፍ የያ-ትውልድ ገበናን እየገለጠ፤ የዛን ዘመን ፖለቲካዊ ሽኩቻ፣ አስተሳሰብና ፍልስፍና ያስኮመኩመናል፡፡ ምንም እንኳን መፅሀፉ በ‹‹ኃይሌ ፊዳ›› እና በመኢሶን (መላው ኢትዮጲያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ ትኩረቱን ቢያደርግም የዘመኑን አስተሳሰብና የትግል ስልት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

በጊዜው ከነበሩት ፖለቲከኞች ብዙዎቹ በዘመኑ የነበረውን ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ እውቀት የቀሰሙ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ በዕውቀት የሚታሙ አልነበሩም፡፡ የንባብ ልምዳቸው የዳበረ፣ የማርክሲዝምና የሌኒንዝም ፖለቲካዊ ፍልስፍና የተጋቱ ምርጦች ነበሩ፡፡ በዛው ልክ ደግሞ በሴራ የተጠላለፉ፣ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ የተካኑ፣ እርስበርስ መተማመን ያልነበራቸው፣ ለሁለት ቡድን የሚሰሩ፤ ሃይል ወዳለው የሚያጋድሉ፣ ለግል ስልጣንና ጥቅም ፍለጋ ወንድማቸውን አሳልፈው የሚሰጡም ነበሩ፡፡

የዚህ መፅሐፍ ፀሐፊ ግን የመጽሐፋቸውን ዋና ትኩረት ያደረጉት አንድ ሰው ላይ ነው፡፡ ይህ ሰው በፖለቲካ ብስለቱ ወደር የማይገኝለት፣ በአዳማጭነቱ የተለየ፣ ነገሮችን በአራት አቅጣጫ መላልሶ የሚመረምር ብልህ፣ አንባቢና መርማሪ፤ ንቁና ብሩህ አዕምሮ የታደለ ወጣት እንደነበረ ፀሐፊው ይነግሩናል፡፡ በተለይ ስለአውሮፓ ባህልና ስልጣኔ (ዝመና) ለማወቅ ከዚህ ሰው ጋር መገናኘት ግድ ነው ይሉናል፡፡ ይህ ሰው ወለጋ ክ/ሀገር እትብቱ የተቀበረው፣ ጄኔራል ዊንጌት የተማረው፤ በአ/አ ዩንቨርስቲ የተመረቀው፤ አውሮፓ ተምሮ ወደሐገሩ የተመለሰው፤ የመኢሶን መስራችና ከመሪዎች አንዱ የነበረው፤ በ37 ዓመቱ ደርግ የገደለው ኃይሌ ፊዳ ነው፡፡

See also  ጎባጢት ድልድይ

ኃይሌ ፊዳ ለወገኑ መወገኑን፣ ለእኩልነት መቆሙን፣ በተለይ የሶሻሊዝም ስርዓት በሐገራችን እንዲፀና መታገሉን፣ እንዲሁም የሐገሩ ጉዳይ ከትዳሩና ከሕይወቱ መብለጡን ሲገልጽ፡-

‹‹እኔ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነፃነትና በሶሻሊዝም ላይ ለቆመ የእኩልነት ሥርዓት መመስረት የገባሁበት ትግል ከሁሉም በላይ ትርጉም ያለውና ከራሴም ሕይወት ጭምር የሚበልጥ መሆኑን እንጂ ማንኛውም ፈረንሣይ ሐገር የሚኖር የውጪ ሰው ያለውዴታው የሚሠራውን ዝቅተኛና የተናቀ ሥራ ሠርቼ ለልጆቼ የዕለት ቀለብ ማቅረብ አቅቶኝ አይደለም፡፡››… ይላል፡፡ (ገፅ – 59)

በየዘመኑ ‹‹መሆን›› ወይም ‹‹ሆኖ መገኘት›› ዳገት የሆነባቸው መምሰልን የሚያጌጡ ‹‹መሳዮች›› ይነሳሉ፡፡ በዚህ ዘመንም የሚመስሉ ሲበዙ የሚሆኑ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ወርቅ ቅቦች እንጂ ወርቆች በቀላሉ አይገኙም፡፡ መምሰል መሆን አይደለምና፡፡ በከተማችን እስካርፍን የአርቲስትነት መለያ ያደረጉ፣ ፀጉርን ማሳደግና መጎንጎን (ድሬድነትን) የሠዓሊነት ምልክት በማድረግ ፀጉራቸውን የሚያሳድጉ ብዙ ናቸው፡፡ አንባቢ ነኝ ለማለት መፅሐፍ ከእጃቸው የማይጠፋ (Book carriers) ነገር ግን የያዙትን መፅሐፍ ያላነበቡ ወይም አንብበው ያልተረዱ ቀላል ቁጥር የላቸውም፡፡ በያ-ትውልድም አብዮታውያን ለመምሰል መቆሸሽና ፀጉር ማንጨባረር የተለመደ ነበር፡፡ በእርግጥ እስካርፍ የሚያዘወትር ሁሉ አርቲስት አይደለም እያልኩኝ አይደለም፡፡ መፅሐፍ ከእጁ የማይጠፋ ሁሉ አያነብም ለማለት አይቃጣኝም፡፡ ያንጨባረረ ሁሉ አብዮታዊ አይሆንም የሚል ድምዳሜም የለም፡፡ ፡ ነገር ግን በመሃል አንዳንዶች የሚመስሉ ነገር ግን ያልሆኑ መኖራቸው እሙን ነው፡፡ የዚህ መፅሐፍ ፀሐፊም ኃይሌ ፊዳ መከረኝ ያሉት ይሄንኑ ነው፡፡ አብዮታዊ ለመሆን መቆሸሽና ፀጉር ማንጨብረር ግድ አለመሆኑን፡፡

ሌላው ፀሐፊው በገፅ 155 ላይ እንደሚነግሩን የአብዮቱ መሪ የነበሩት ኮሌኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሚያዚያ 1969 ዓ.ም. ለቀይ ኮከብ ዘመቻ የተዘጋጀውን የሰለጠነ ሕዝባዊ ሰራዊት ለመሸኘት በተጠራው ሰልፍ ላይ ወርውረው ስለሰበሯቸው ሶስት በቀለም የተሞሉ የፋሽኮ ጠርሙሶች ጉዳይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጠርሙስ የኢምፔሪያሊዝምን ደም እንዴት እንደሚያፈሱ የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ያካባቢው አድሃሪ የሚሏቸውን የአረብ ሐገራትን የሚመለከት ነበር፤ ሶስተኛው ደግሞ በቢሮክራሲ ውስጥ የተሰገሰጉትን የውሰጥ ጠላቶቻቸውን ደም እንዴት እንደሚያፈሱት የሚያሳይ ነበር፡፡ ነገር ግን ከወረወሯቸው ጠርሙሶች ሁለቱ ሲሰበሩ ሶስተኛው ጠርሙስ ግን አልተሰበረም ነበር፡፡ ኃይሌ ፊዳም ይሄን በተመለከተ በፌዝ መልክ ኮሌኔሉን እንዲህ ብሏቸዋል፡-

See also  የአገር ደህንነት - በትህነግና ሌሎች ሽብርተኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላ

‹‹ጓድ ሊቀመንበር ቢሮክራሲው ብቻ ነው የተረፈው፡፡ የራሱ የቢሮክራሲው አሻጥር ይሆን እንዴ? ያቀበለዎት ጠርሙስ ሳይሆን በፕላስቲክ የተሞላ ቀይ ቀለም ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንደው ፍንክች አላለም፡፡ የቢሮክራሲው አሻጥር ሳይሆን አይቀርም፡፡››(ገፅ – 155)…. በማለት ቀልድ የሚመስል ምር ተናግሯቸዋል፡፡

አዎ! ዛሬም ትናንትም መልካም መሪዎችን የሚጥለው የውጪ ጠላት ሳይሆን በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰገው ሆዳምና ስልጣን ፈላጊው ነው፡፡ የፖለቲካ አሻጥር የሀገር ዕድገትን ያሽመደምዳል፡፡ ዘረኝነት አንደኛው አሻጥር ነው፡፡ በብሔር ተዋፅኦ ሹመኞችን መሾም ኋላቀር አሰራር ነው፡፡ ብቃት፣ ንቃት፣ ጥበብ የሌለው መሪ አይደለም ሐገር ራሱን መምራት አይችልም፡፡ የእኛ ሐገር ፖለቲከኞች ጥቅም ለማጋበስ፤ ሐገር ለመበዝበዝ ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ሕገ መንግስት አፀደቁ፡፡ ይኸው ዛሬም ወደኋላ 40 ዓመት ተመልሰናል፡፡ ከያ-ትውልድ የትግልና የፖለቲካ ስልት ፈቀቅ ያላልነውና አዲስ መንገድ ያላበጀነው ሐገራችን የምትመራበት ሕገመንግስት ሐገርን የሚያቆም ሳይሆን የሚበታትን በመሆኑ ነው፡፡ አሻጥሩን ማስወገድ፤ ሴራውን መንቀል አልቻልንም፡፡

ወዳጄ ሆይ… መፅሐፉን አንብበውና ዘመንህን ከያ-ትውልድ ዘመን ጋር አስተያየው፣ አነፃፅረው፡፡ የሚወሰደውን ውሰድ. የሚጣለውን ጣል፡፡ መደገም የሌለበትን አትድገም፡፡ የዛ-ትውልድን ታሪክ ማወቅ ያሁኑን ዘመን ለመለለወጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ትናንት ባልሰራና በከሸፈ የፖለቲካ መፍትሄ ዛሬም ሐገርን ማዳን አይቻልም፡፡ ትርፉ አዙሪት ብቻ ነው!

አዲስ አብዮት አምጣ፣

አዲስ ጥበብ አውጣ!

ከአዙሪትህ ቶሎ እንድትወጣ፡፡

ታሪክ ስራ የማይረሳ፣

ዝንተዓለም የሚወሳ፣

መገዳደልን ድል የሚነሳ፡፡

መልካም ንባብ!

ኢትዮጵያዊነት ሰው’ነት ነው!

ቸር ጊዜ!

____________________

እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

ቅዳሜ የካቲት ፲፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.

Via – book for alm

Leave a Reply