ETHIO12.COM

የ80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ

በበዓሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው አባቶቻችን እና እናቶች በከፈሉት መሰዋእትነት ነው ብለዋል።

በጊዜው የነበሩት አርበኞቻችን ታላቅ ነበሩ፤ ሀገር መገንባት ከባድ ነው ማፍረስ ግን ቀላል ነው፤ ሁሉም ሀገሩን መጠበቅ አለበት ነው ያሉት።

ልጅ ዳንኤል ጆቴ ሰላም በቀላሉ አይገኝም፤ ችግሮች የትም አሉ፤ የኛ ችግር የሚነሳው ግን ከቅጥረኞች ነው፤ ሀገር በማፍረስ ታሪካችን ለማጥፋት የሚሠሩትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ቆመን ልንታገላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይ ወጣቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመሻገር በአንድነት መቆም አለባቸውም ብለዋል።

የ80ኛው ዓመት የአርበኞች የድል በዓል በድምቀት እንዲከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ላደረገው አስታውፆዖም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ልጅ ዳንኤል ጆቴ።

የህዳሴ ግድብ ላይ እየተቃጣ ያለውን ዛቻና ዘመቻ የምንመክተው በጋራ በመቆም እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ወራሪው ጣሊያን የአድዋ ሽንፈቱን ለመመለስ በድጋሜ ያደረገውን ወረራ አባቶቻችን አይበገሬነታቸውን ዳግም ያስመሰከሩበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

ጀግኖች አባቶችና እናቶች በጀግንነት ሀገራቸውን ያስከበሩት በአንድነት በመቆማቸው ነው፤ ይህ ትውልድም ዛሬ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ አድርገውናል ነው ያሉት። ከእነሱ አንድነትንና ጥበባቸውን መማር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከጀግኖች አርበኞቻችን በመማር በአንድነት ከቆምን ትውልዱ ታሪክ የማይሰራበት ምክንያት የለም ብለዋል።

ለጀግኖች አርበኞቻችን ክብር ይገባቸዋል ያሉት ምክትል ከንቲበዋ ለአባቶችና እናቶች ከዚህ በኋላ በከተማ አስተዳደሩ በነጻ ህክምና እንዲያገኙ መወሰኑንም አብስረዋል።

በበዓሉም የፌዴራል ፖሊስ የመከላከያ ማርሽ ባንድ አባላት የተለያዬ ጣእመ ዜማዎችን አሰምተዋል። በወጣቶችም ሽለላና ቀረርቶ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:– ጋሻው ፈንታሁን– ከአዲስ አበባ (አሚኮ)

Exit mobile version