Site icon ETHIO12.COM

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትናንት ለተፈጠረው የአደባባይ ኢፍጣር መርሐግብር መስተጓጎል ይቅርታ ጠየቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ትናንት ለተፈጠረው ነገር በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።የኢትዮጵያ አደባባዮች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አንድ ማዕድ በጋራ የተቋደሰ ህዝብ የኔ፣ የኔ በሚል በአንድ አደባባይ አይጣላም ሲሉ አክለዋል፡፡

“የአደባባይ ኢፍጣር መርሐግብሩ የተስየጓጎለው ወቅታዊ የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የቦታው ስፋት እና ርዝመት ውስን እንዲሆን ባቀረብነው ሀሳብ አዘጋጅ ኮሚቴው ባለማመኑ ብቻ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።

የትናንት ምሽቱ የጸጥታ አካላት እንቅስቃሴም የሁሉም ነዋሪዎች ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ያለመ እንጂ በፍፁም የኢፍጣር ክልከላ አለመሆኑን ገልፀዋል።በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሌሎች የኢፍጣር መርሐግብሮች መካሄዳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

“ይሁን እንጂ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት ይህን ጉዳይ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ ሊያራግቡት ሞክረዋል” ነው ያሉት ወ/ሮ አዳነች። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማውን ቅሬታ የገለጸበት መንገድ ጨዋነት የተሞላበት እና ሰላማዊ እንደነበር በመግለፅ ምክትል ከንቲባዋ አድናቆታቸውን ችረዋል።


Exit mobile version