ETHIO12.COM

ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች

ቻይና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገልጻለች። በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የልዑክ ኃላፊ ዢ ቲያን ግድቡ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ቀልብ የሳበ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ መነሳቱን አስታውሰዋል። ቻይና እንደአንድ የአፍሪካ ወዳጅ ሀገር ግድቡ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ትረዳለች ብለዋል። በመሆኑም በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ግድቡን በተመለከተ የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር ቻይና እንደምትግፍ ገልጸዋል። “ቻይና የአፍሪካ ሀገራት ወዳጅ እንደመሆኗ ግድቡ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው እንረዳለን፤ በተለይም ደግሞ ለኢትዮጵያ ልማት ያለውን ጠቀሜታ እናውቃለን” ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ግድቡን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሦስቱ ሀገራት የሚያካሂዱትን ድርድር ትደግፋለች ብለዋል። “አፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ግድቡን በተመለከተ የሚካሄደውን ድርድር እንደግፋለን፤ በውይይት መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ትክክለኛ መንገድ ነው፤ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርሕም እንደግፋለን” ሲሉም ተናግረዋል።

“የአፍሪካ ኅብረት ለግድቡ ሁነኛ መፍትሔ ለመስጠት አመቺ አውድ ነው፤ ስለዚህም የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ኅብረት መያዙን እንደግፋለን” ነው ያሉት ኃላፊው።ቻይና ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የአፍሪካ ኅብረት ከሚያካሂደው ድርድር እንዳይወጡ እና ልዩነቱም በውይይት እንዲፈታ ታበረታታለች ብለዋል። ቻይና በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር መደገፏ ይታወሳል።

EBC

Exit mobile version