ሩሲያ በግድቡ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር እንዲፈቱ እንደምትደግፍ አስታወቀች


በግብጽ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ያደረጉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከግብጽ አቻቸው ሳሚ ሽኩሪ ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ሳሚ ሽኩሪ ኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊትን ለማከናወን ማቃዷን በማጣቀስ “የተናጠል እርምጃ እንዳይወሰድ ሩሲያ ጫና እንደምታሳድር እንትማመናለን” በሚል ቢናገሩም፤ የሩሲያው አቻቸው በተቃራኒው አገራቸው የአፍሪካ ህብረትን የድርድር መንገድ እንደመትደግፍ አስታውቀዋል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ሩሲያ በሶስቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር አልተጋበዘችም። ይሁን እንጂ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር የሚካሄደውን ድርድር ደግፋለች፤ ትደግፋለችም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባው ገልጿል።

በሶስት አገራት መካከል ያለውንና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን አለመግባባት ለመፍታት መፍትሄው በአፍሪካ ህብረት መሪነት እየተካሄደ ያለው ድርድር መሆኑን የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በአጽንኦት ተናግረዋል።. (ኢ ፕ ድ)


Leave a Reply