Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ህዝብ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታና፣ መውጫ መንገዱን ማሰብ፣ የህሊና ዕረፍትንና የመንፈስ ሠላምን የሚነሳ ነው።

የምሬን ነው የምላችሁ፣

በትግራይ ህዝብ የገባበት መከራና አበሳ ከፍተኛ ሀዘንና ቁጭት የሚፈጥር ነው። ይህ እንዳይሆን መጮህ የጀመርነው፣ ገና ዱሮ ህወሓት በሥልጣን ላይ እያለ ነበር። የትግራይ ህዝብ፣ የህወሓትን አፋኝ አገዛዝ ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ውስጥ፣ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት፣ ቢያንስ የህወሓት መደበቂያ ምሽግ እንዳይሆን ያለማቋረጥ ወትውተን ነበር።

ሆኖም ግን፣ ህወሓት የህዝብ ግፊትና ጫና በፈጠረው የውስጥ (ድርጅታዊ) ትግል፣ ያለተቀናቃኝ ከተቆጣጠረው ሥልጣን ወደዳር ሲገፋ፣ ወይም በልኩ እንዲኖር ሲደረግ፣ “ለምን ተነካሁ?” በሚል አኩርፎና የጥፋት ሴራውን ፀንሶ፣ ወደ መቀሌ – ትግራይ ነበር ያፈገፈገው። ዱሮም ቢሆን፣ የትግራይን ህዝብ መያዣ (hostage) አድርጎ የያዘው፣ እንዲህ የቁርጡ ቀን ሲመጣ መደበቂያ ሊያደርገው ነበር። ህወሓት ሊታረቅ የማይችል የጠላትነትና/የአጥፊና ጠፊነት ትርክትን በማስረፅ፣ የትግራይ ህዝብ ሌሎችን በጥርጣሬና በሥጋት እንዲያይና፣ ህወሓትን የህልውናው መከታና የመጨረሻ ዋስትናው አድርጎ እንዲያስብ፣ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ያህል ያለማቋረጥና ያለመታከት ሠርቷል። በዚያ ላይ፣ አስተሳሰቡን በኃይል ለመጫንና፣ እንዲሁም ከሥርዓቱ ሊያፈነግጡ የሚችሉ “ትግራዋይን” ለመቆጣጠር የዘረጋው የአፈና መረብና የፖለቲካ መዋቅር፣ በቀላሉ ሊበጣጠስ/ሊፈራርስ ይችላል ተብሎ የሚገመት አልነበረም። በርግጥ ቀድሞ እንደተገመተውና እንደተፈራው ባይሆንም፣ አሁን ህግና ሥርዓትን ለማስከበርና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ህወሓት በትግራይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም፣ የጥፋት መረቡን ሊዘረጋ እንደሚችል ቀድሞም የሚገመት ነበር። አሁን በተለያዬ ሥም የሚንቀሳቀሱና፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ አረመኔያዊ ግድያ፣ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ የዘር ፍጅትና፣ መጠነ-ሰፊ የማፈናቀል ድርጊት ከሚፈፅሙ ኃይሎች ጀርባ፣ የህወሓት እጅ እንደሚኖርበት ጥርጥር የለውም። የህወሓት አፋኝ ቡድን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካል የሆነውን ሰሜን ዕዝን በመምታት በፈፀመው ስትራቴጂያዊ ስህተት ሳቢያ፣ ትግራይ ላይ አከርካሪው ቢመታም፣ ቀደም ብሎ በሌሎች አካባቢዎች የዘረጋውን የጥፋት መረብና/መዋቅር ሊጠቀም እንደሚችል እሙን ነው። ዓላማው፣ አንድም፣ በተለይ በአማራና ኦሮሞ መካከል በቀላሉ ሊታረቅ የማይችል ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ፣ (የዚህ አርክቴክቶች እነጌታቸው ረዳ በህይወት መኖራቸውን ልብ ይሏል) ሁለትም፣ በየቦታው የፀጥታ ሥጋትና ውጥረቴ በመፍጠር፣ የመንግሥትን ኃይል መበታተንና በትግራይ የተሰማራው ኃይል እንዲመናመን ማድረግ፣ ሦስተኛ፣ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ የተፈጠረውን ብጥብጥና አለመረጋጋት የመቆጣጠር አቅምና ብቃት እንደሌለው ማሳዬትና፣ ከዚህ አንፃር፣ ህወሓትና ግብረ-አበሮቹን አማራጭ ኃይል አድርጎ ማቅረብ ነው።

ሆኖም ግን፣ በተለይ ህወሓት እንዳሰበው፣ አማራጭ ኃይል ሆኖ ወደ ሥልጣን መመለስ ቀላልና የሚሳካ ግብ አይደለም። ዛሬ ላይ፣ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የሸዋ፣ የአፋርና … የሌሎችም አካባቢዎች ህዝብ፣ እንደዱሮው ህወሓትን አዝሎና አጅቦ አራት ኪሎ ሊያስገባ የሚችልበት ሁኔታና ምክንያት የለም። ህወሓት ይህን ነባራዊ ሁኔታ/ሐቅ በቅጡ በመረዳት፣ ከዚያ በመለስ ትግራይን ማዕከል ያደረገ ግብ ይኖረዋል ተብሎም አይታሰብም። አንዳንድ የህወሓት ግርፎች፣ “ትግራይን ነፃ ማውጣትና ራሷን የቻለች ሀገር ማድረግ” በሚል ቀቢፀ-ተስፋ፣ የሚያሰሙት ቀረርቶና ፉከራም፣ የትግራይን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሊያረጋግጥ የሚችል እንዳልሆነ ይታወቃል።

የትግራይ ህዝብ፣ በህወሓት የጥፋት መንገድ፣ ብዙ ርቀት ሊሄድና አትራፊ ሊሆን እንደማይችል፣ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እስካሁን ድረስም፣ ግማሽ ምዕተ-ዓመት በፈጀው የጥፋት ጉዞ፣ የትግራይ ህዝብ ያተረፈው ነገር የለም። ያተረፈው ነገር ቢኖር፣ ውድ ልጆቹን ለጦርነት መገበርና፣ ከሌላው ወገኑ ጋር የጠላትነት ስሜት መፍጠር ብቻ ነው። ምናልባት ግን፣ ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ፣ ጥቂቶች አዛዥ – ናዛዥ መሆን፣ የሀገሪቷን አንጡራ ሀብት በግላጭ መቀራመትና/ማግበስበስና፣ በአቋራጭ መክበርና ቱጃር መሆን ችለው ይሆናል። ይኸ ግን፣ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ያለፈበትንና/ያለበትን፣ አሁናዊ የኑሮ ሁኔታውን የሚገልፅ አይደለም። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ፣ በአስከፊ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር፣ ህግና ሥርዓትን ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ ተረጋግጧል። ህዝቡ ቢያንስ ለሁለትና ሦስት ወራት ራሱን መመገብ የሚያስችል ጥሪት እንደሌለው በይፋ ታውቋል። ዛሬ ላይ፣ የትግራይ ህዝብ፣ ለከፍተኛ ችግርና ርሀብ መጋለጡ፣ ከእኛ አልፎ የዓለም መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።

የትግራይ ህዝብ እስካሁን ለደረሰበት መከራ፣ ችግርና ርሀብ መንስኤውና/ተጠያቂው ህወሓት መሆኑን አይገነዘብም ማለት ይቻል ይሆን? አሁንስ ቢሆን፣ የህወሓት ርዝራዦች “ከወደቁ ወዲያ በመንፈራገጥ – አጉል ከመላላጥ” ባለፈ፣ የሚያሳኩት ግብ ይኖራል ተብሎ ይታሰብ ይሆን? ካልሆነ፣ ህዝቡ እነዚህን “ወንጀለኞች” ነጥሎና ከውስጡ መንጥሮ በማውጣት፣ ለምን አሳልፎ አይሰጣቸውም? ለጥቂቶች ያልተገራ ፍላጎት፣ የበዛ ራስ ወዳድነትና፣ አጉል እልኸኝነት፣ ወይም “አልተሸነፍንም” ለሚል የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ፣ ህዝቡ ይህን ሁሉ ዋጋ ለምን ይከፍላል? ብዙ ሊያነጋግር የሚችል አጀንዳ ሊሆን ይችላል።

እንደሚታወቀው፣ ህወሓት ያደራጀው “የትግራይ ልዩ ኃይል” ሲመታ፣ ወታደራዊ ዩኒፎርሙን አውልቆ/ጥሎ፣ ትጥቁን ሳይፈታ፣ ወደህዝቡ ነው የተበተነው። ወደህዝቡ የተበተነው ኃይል ትንሽ ፋታ ሲወስድና፣ የተበጣጠሰውን የጥፋት መረብ ክሮች ሲያገኝ፣ በሀገር መከላከያ ኃይሉ ላይ የደፈጣ ጥቃቶችን መሰንዘሩና፣ ተመልሶ/ሩጦ ወደህዝቡ መግባቱ አልቀረም። ሲቪል ለብሶ የደፈጣ ጥቃት በመሰንዘር ከተሳካለት፣ የትግራይ አክቲቪስትች ጭፈራና ቀረርቶ አይጣል ነው። የመከላከያ ኃይሉ፣ ራሱን ለመከላከል በሚወስደው እርምጃ፣ የህወሓት ጭፍራዎች ከተደመሰሱ፣ “በሲቪሊያን ላይ የተፈፀመ ጥቃትና፣ የዘር ፍጅት ነው” በሚል እየያቸውን ያቀልጡታል፤ ጩኸታቸው በመላው ዓለም ያስተጋባል። ዓላማቸውም፣ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጆሮ እንዲሰጣቸውና፣ የአብይ አህመድን መንግሥት በሰብኣዊ መብት ጥሰትና በጦር ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ነው። ሆኖም ግን፣ ጩኸት ተፈርቶ እንደሀገር፣ ህግና ሥርዓትን ለማስከበርና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሊቆም የሚችልበት አግባብና ምክንያት አይኖርም።

ይህም ሆኖ ግን፣ የትግራይ ህዝብ የገባበት መከራና አበሳ በጣም አሳሳቢና የህሊና ዕረፍትን የሚነሳ ነው። “ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ህወሓት ነው” በሚል ብቻ፣ ሌላው ቢቀር ከሞራላዊ ኃላፊነት መሸሽ አይቻልም። ስለሆነም፣ ህግና ሥርዓትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ፣ በተቻለ መጠን የንፁሃን ዜጎችን ህይወት፣ ደህንነትና መብት አደጋ ላይ የማይጥል ስለመሆኑ በየጊዜው መገምገምና፣ የትግራይ ህዝብን መከራ ለመቀነስ የሚያስችሉ ስልቶችን መቀየስ ያስፈልጋል። ከዚሁ በተጓዳኝ፣ ህግና ሥርዓትን በማስከበሩ ሂደት፣ ሆን ብለው በንፁሃን ላይ ያነጣጠሩ፣ ህይወት ያጠፉና የአሰገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀሙ የህግ አሰከባሪው ኃይል አባላት ካሉ፣ በአግባቡ ተለይተው ለህግ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ይህም በገለልተኛ አካላት (በሰብኣዊ መብት ተቋማት) በመጣራት ላይ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል።

በሌላ በኩል፣ የህወሓት ርዝራዦች ሆን ብለው መንግሥትን ለማሳጣት፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፅሟቸውን ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች በሚገባ ተከታትሎ ማጋለጥ፣ በተለይ የትግራይ ህዝብ በደንብ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል። ምናልባትም፣ “ይህን የህወሓት አደገኛ ሴራ፣ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት ላላነሰ ረጅም ጊዜ አብሮት የኖረው የትግራይ ህዝብ አያውቅም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ሆኖም ግን፣ አሁንም ቢሆን፣ በትግራይ ህዝብ ዘንድ ብዥታ ካለ፣ እስከ ጥግ ሂዶ በደንብ ማጥራት ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ፣ የትግራይ ህዝብ ምን ሊሰማው እንደሚችል፣ በእሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ ያስፈልጋል።

ይህም ሆኖ፣ የትግራይ ህዝብ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታና፣ መውጫ መንገዱን ማሰብ፣ የህሊና ዕረፍትንና የመንፈስ ሠላምን የሚነሳ ነው።

ለዛሬው ይብቃኝ፤
እንዳውም ሳላውቀው አሰፋሁት – አይደል?
የመሐመድ ኣሊ እይታወች. Via – zoba temben

Exit mobile version