ETHIO12.COM

ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው

“የዴሞክራሲ ቁንጮ ነን” የሚሉት ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ አቋም እያራመዱ እንደሚገኙ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በምርጫው ኢትዮጵያን ማሻገርና አሸናፊ ማድረግ ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሠላምና መረጋጋት ሁኔታ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውይይቱ የተካሄደባቸው አጀንዳዎች ናቸው።

ተወያዮቹ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እጅ ለመጠምዘዝ የሚያደርጉት ጥረት ከዴሞክራሲ መርሃቸው ጋር የሚቃረን መሆኑን ገልጸዋል። ምዕራባዊያኑ በተለያዩ አገራት ጉዳዮች አድሏዊና መርህን ያልጠበቁ አቋሞችን እንደሚያንጸባርቁና በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ያለው አካሄድም ከዚሁ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ አገራት ‘ለእናንተ የምንወስነው እኛ ነን፣ የምንለውን መከተል አለባችሁ’ እያሉ እንደሆነና ይህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚነካ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ እንደሆነ ገልጸዋል።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

በኢትዮጵያ ላይ ጫናው የበረታው ተስፋ ያላትና እያደገች ያለች አገር በመሆኗ፤ እየተጓዘችበት ያለው ጎዳና ከቀጣናው አልፎ በአፍሪካ ሊኖራት የሚችለው ተጽእኖ ይጨምራል በሚል ስጋት እንትዳከም ለማድረግ እንደሆነም ነው ተወያዮቹ የተናገሩት። ከስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር በተያያዘም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና አሸናፊነት በላይ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ትልቁ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምርጫው ኢትዮጵያን ለመገንባትና ህልውናዋን ለማስቀጠል እንደ መሸጋገሪያ የሚታይ እንደሆነና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በዚሁ እሳቤ መንቀሳቀስ እንደሚገባችው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ምርጫውን የምታካሂደው ሁሉም ሁኔታ ምቹ ሆኖ ሳይሆን አገሪቷን ለማሻገር አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ እንደሆነም የውይይቱ ተሳፊዎች አመልክተዋል። ምርጫው ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

Related stories   ሰላም፣እርጋታና የዜጎች ደህንነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው – በአሜሪካ የህዝብ ዲፕሎማሲ አማካሪ ምክር ቤት

በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ እየመጡ ያሉ ጫናዎችን ለመቋቋም ሕዝብን ከፊት ያስቀደመ የንቅናቄ ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ነው ተወያዮቹ የጠቆሙት።

መንግስት ሕዝቡን በማሳተፍ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያላት አቋም በግልጽ እንዲተላለፍ የማድረግ ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። በግድቡ ግንባታ ላይ ጫና ለማድረግ ለሚሞክሩ አካላት ኢትዮጵያ ከያዘችው አቋም ፈቀቅ እንደማትል በጥብቅ ማስገንዘብ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


Exit mobile version