ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ” ወግድ አለች” መንግስት መግለጫ ሰጠ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአንዳንድ አጋር አካላትና የሚዲያ ተቋማት በአገሪቱ ላይ እየቀረቡ ያሉት ውንጀላዎችን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ በውስጥ ጉዳይዋ ከየትኛውም የውጭ አካላት ምንም ዓይነት መመሪያ እንደማትቀበል በግልጽ አስታውቋል፡፡

በተደጋጋሚ ማቆሚያ የሌለው ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ላይ ያተኮሩ ፍትሓዊ ያልሆኑ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ መንግስት አጋር አካላት ለሚያሳስባቸው ጉዳዮች አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠ ቢሆንም አንዳንድ አካላት ከውንጀላ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንዳልቻሉም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።፡

የዳበረ ዴሞክራሲና የፖለቲካ ባህል ግንባታ አገር በቀል ሂደት እንጂ፣ በውጭ ጫና የሚሳካ እንዳልሆነ ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል። አንዳንድ የኢትዮጵያ አጋሮች ኢትዮጵያ ከጋጠሟት ችግሮች ለመላቀቅ የምታደርጋቸው ጥረቶች ከመርዳትና ከመደገፍ ይልቅ ሁኔታውን ማባባስ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ገልጿል። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ በድጋሜ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አቋሟን ግልጽ ለማድረግ ተገዳለች።

Related stories   የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማ- በተወነችው ተውኔት ውስጥ ዳግም ሞት የተፈረደባቸው ዜጎች

የትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ቁርጠኝነቱን መግለጹ ብቻ ሳይሆን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች ያለ ምንም ገደብ በክልሉ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉን ሚኒስቴሩ በድጋሚ አስታውሷል። አያይዞም በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ የነበረበት ሁኔታ ቢኖርም ችግሩ አሁን መፈታቱን አመልክቷል።

ሚኒስቴሩ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን ገልጾ፣ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮችን ያቀፈ ቡድን በትግራይ ክልል ተሰማርቶ የምርመራውን ስራ እየሰራ መሆኑን ሁሉም እንደሚያውቁት ጠቁሟል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የማይካድራ ጭፍጨፋን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ ሪፖርት እያደረገ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠርና፣ መንግስት ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ግልጽ፣ እና ተአማኒ በሆነ መልኩ እንዲከናወን፣ በአገሪቱ ዛለቂ ሰላም፣ ነፃነትና ዴሞክራሲ እንዲኖር ለማድርግ እየሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

Related stories   ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማጣራቱ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን እንደሚያካትት አስታወቀ፤ መንግስትና አማራ ክልል በማይካድራ ጉዳይ ተኝተዋል

ዛሬም ሆነ በማናቸውም ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ ኃይሉን ያለ ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ማሰማራት እንደሚችል በመግለጫው በግልጽ ተነግሯል። የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት እንደወትሮው ሁሉ ክፍትና በጋራ ጥቅም ላይ ተመስርቶ የሚከናወን መሆኑንን ግልጽ አድርጓል።

ሕዝብ የቀደመውን የአርበኝነት ስሜት እየተላበሰና አገሩ ላይ እየተከናወነ ያለው ዘመቻ ግልጽ እየሆነለት መምጣቱ መንግስት ለያዘው ” አሽከር አልሆንም” አቋም ከፍተኛ ድጋፍ እየሆነ መምጣቱን አስተያየት ሰጪዎች ሰሞኑንን ሲናገሩ ነበር።


Exit mobile version