Site icon ETHIO12.COM

በሀዋሳ ጉሙሩክ ጣቢያ ሁለት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ተያዙ


የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በሀዋሳ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩ ሁለት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች መያዙን አስታወቀ፡፡

በሀዋሳ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እያንዳንዳቸው 64 ሲም ካርዶችን የሚይዙ ሁለት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች እና ለዚሁ እኩይ ተግባር ማስፈጸሚያነት የሚውሉ የተለያዩ አጋዥ መሣሪያዎች መያዛቸውን በኢመደኤ የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ክፍል የእውቀት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ገ/መስቀል ገልጸዋል፡፡

የቴሌኮም ማጭበርበርያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት ብዙ ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሆነና የሚያስመጧቸውም የራሳቸውን የኢኮኖሚ ትርፍ መሠረት አድርገው የሚሰሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መሆናቸውን አቶ አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

በኤጀንሲው የሴኩሪቲ ክሊራንስ ማዕከል የቁጥጥርና ክትትል ኃላፊ አቶ ሙህዲን ተማም በበኩላቸው የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎቹ ወደሀገር ውስጥ ገብተው ለመጡበት ዓላማ ውለው ቢሆን ኖሮ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱ እንደነበረ አውስተው ኤጀንሲው በሰራው ስራ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 19 ሚሊዮን ብር የሀገር ሀብትን ከኪሳራ መታደግ መቻሉን መናገራቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ via EBC

Exit mobile version