በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ያልተፈቀዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የቴሌኮም ማጭበርበሪያ /ፍራዉድ/ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ መያዙን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲዉ በ2013 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ የጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ስምንት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ዉስጥ ሊገቡ ሲሉ መያዙን የጠቀሰው ኤጀንሲው፤ በሀገር ደረጃ ሊያደርስ የነበረዉን ከ19.3 ሚሊዮን ብር በላይ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳን መቻሉን በኤጀንሲዉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊዉ አቶ እሸቱ ቡሬሳ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀዉ በጀት አመት የደህንነት ስጋታቸዉ ከፍተኛ የሆኑ በ14 ድርጅቶች ስም የመጡ 49 ድሮኖችና የስለላ ካሜራዎች ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ መከልከላከል መቻልንም ኃላፊው ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች መካከልም የቴሌኮም ፍራዉድ መፈጸም የሚያስችል (sim box) ፣ ስፓይ ካሜራ፣ ሳተላይት ስልክ፣ ድሮን ፣ የመገናኛ ሬዲዮ፣ ወታደራዊ ባይነኩላር እና የቅኝት መሳሪያዎች፣ ለሰቪላዊና ወታደራዊ አገልግሎት የሚዉሉ ጂፒኤሶች፣ ድብቅ የድምፅ መቅጃ ማይክራፎኖች፣ ዱዋል ባንድ ራዉተር፣ Transmitters (fm) እና vsat የተባሉት እንደሚገኙበት ነው የተጠቀሰው።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት አስመጭዎችም ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ዓይነት በመለየት ማስመጣት እንደሚገባቸዉ ኃላፊዉ አሳስበዋል።

ኢንፎርሜሽን መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና ከሀገር ውጪ የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች፣ የመረጃ ማነፍነፊያዎችና የጥቃት መፈጸሚያ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ደህንነት ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ የመከላከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበትም ከኤጀንሲው ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply