ETHIO12.COM

ድህረ ደርግና የኮሎኔሉ ሽሽት

ያሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ የዓለማችን ክፍለ ሀገራት ታላላቅ ታሪኮች የተከሰቱበት ነው:: ይህ እውነት በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው። በተለይ በያዝነው የግንቦት ወር ሊታወሱ የሚገባቸው የታሪክ ዘለላዎች በርካታ ናቸው።

ከእነዚህ ሁነቶችና ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ለዛሬ የደርግ ኢሰፓ መንግስት ፕሬዚዳንት በመሆን በርካታ አመታትን የዘለቁት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም በትረ ስልጣናቸውን ትተው ከአገር የሸሹበት ግንቦት 13 ቀን 1983 ይጠቀሳል:: እኛም ለዚህ ታሪክ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን አገላብጠን በማጥራት ታሪኩን ወደኋላ ተመልሳችሁ እንድትቃኙ ለማድረግ ሞክረናል ። መልካም ምልሰት።

ድህረ ታሪክ ከ1966 እስከ 1979 ዓ.ም

በ1966 አም የተካሄደውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ደርግ በሚል ይጠራ የነበረው ወታደራዊ አገዛዝ የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥሮ ቆይቷል። ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለስርዓቱ መገለጫነት የተጠቀሙት ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ መሆናቸው ይነገራል:: ይሄውም ሰኔ 21፣ 1966 ዓ.ም. ነበር።

በዚህ ወቅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት አካሂደዋል፤ ሻለቃ ናደው የዚህ ኮሚቴ ማስታወቂያ ጉዳይ ሠራተኛ ነበሩ። ደርግ በዚህ ሁኔታ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች) ከተመሰረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠው ሀገር ጥለው እስከ ሄዱበት ቀን ድረስ/ በተለያየ የስልጣን ስያሜ ይጠሩ የነበረበት ሁኔታ ቢኖርም/ በዚህ ስልጣን ላይ ቆይተዋል።

የታኅሣሥ ግርግር ተብሎ በሚታወቀውና በ1953 ዓ.ም. የተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ የቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ መንግስት የተለያዩ ማሻሻያ ለውጦችን ለስርዓቱ አስተዋውቋል። አብዛኛዎቹ ማሻሻያዎች መፈንቅለ መንግስቱን እንዲደግፉ ለሚጠረጠሩ የጦርና የፖሊስ ሃይሎች የመሬት ስጦታ በማድረግ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ስለሆነም የአገሪቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታ በቋሚ ሁኔታ ሊሻሻል አልቻለም።

በ1958ዓ.ም. የባለ ርስቱን መደብ ሚና ለመቀነስ በማሰብ የዘውዱ ሥርዓት አዲስ አይነት የመሬት ግብር ለማስተዋወቅ ሞከረ። ሆኖም ፓርላማው ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገው። በምትኩ፣ በሚቀጥለው ዓመት የእርሻ ውጤቶች ግብር ለፓርላማ ቀርቦ ጸደቀ።

ምንም እንኳ የጸደቀው ግብር መንግስት ካቀረበው በጣም የተለወጠ ቢሆንም፣ በባለርስቱ መደብ ዘንድ አመጽ ማስነሳቱ አልቀረም። በተለይ በጎጃም ባለርስቶች በተነሳ አመጽ ምክንያት የሁለት አመት ወታደራዊ ዘመቻ በጎጃም ተደርጎ አመጹን ለማሸነፍ ስላልተቻለ መንግስት ወታደሩን ከጎጃም በማውጣት ግብሩን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ ግድ አለው። እንዲያውም ወደኋላ፣ እስከ 1932ዓ.ም. የነበረ የግብር እዳ በሙሉ ተሰረዘ። በስርአቱ ላይ የደረሰው የጎጃሙ ሽንፈት ሌሎች ለውጥን የሚቃወሙ ክፍሎች እንዲያምጹ ከማበረታቱም በላይ ስርዓቱን ለሌላ አጣብቂኝ ዳረገው።

ለውጥን የሚቃወሙ ኃይሎች በሚያምጹበት በዚያው ወቅት፣ በተቃራኒው ለውጥን የሚፈልጉ ተማሪዎች፣ ገበሬዎችና፣ የሰራተኞች ማህበራት ባንጻሩ የኑሮ ውድነትን፣ ጉቦንና፣ የመሬት ሥርዓቱን በመቃወም ማደም ጀመሩ። ይህ የተወሳሰበ ሁኔታ በእድሜ እየገፉ የሄዱት ንጉሱ ፊታቸውን ወደ ውጭ ጉዳይ እንዲያዞሩና የአገሪቱን የውስጥ ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትራቸው አክሊሉ ሃብተወልድ ጫንቃ ላይ እንዲያስቀምጡ አደረጋቸው።

ሥርዓቱ በሁለት ተጻራሪ አጣብቂኞች ውስጥ ገብቶ ባለበት በዚህ ወቅት የተፈጠረው የርሃብ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስናና ያስከተሉት አጠቃላይ ቅሬታ የ1966ቱ አብዮት እንዲፈነዳ ግድ ሆነ። አብዮቱን ሀ ብሎ ከጀመሩት መካከል የወታደሩ መደብ ሲሆን፣ የወታደሩ አመጽ ጥር ወር 1966 ዓ.ም. ነገሌ፣ ሲዳሞ ላይ ሰፍሮ የነበረው የምድር ጦር ሠራዊት አዛዥ መኮንኖቻቸውን ሲያግቱ ይጀምራል። ጉዳዩ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚኖሩ የሰራዊቱ ክፍሎች ድጋፍን በማግኘቱ በወታደሩ መደብ ከመዛመቱም ባሻገር ወደ ተቀረው ዜጋም በመሸጋገሩ በብዙ ከተማዎች አመጽ ይነሳ ጀመር።

የዘውዱ መንግስት ለዚህ መልስ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ብዙ ጥቃቅን ለውጦችን አድርጓል፤ ለምሳሌ አክሊሉ ሃብተወልድን አንስቶ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አደረገ፣ ለወታደሩ ልዩ ደመወዝ ጭማሪ ፈቀደ፣ ሊተገበር የነበር የትምህርት ስርዓት ማሻሻያ ለውጥን በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት አስቆመ፣ የካቲት ወር ላይ እንዲሁ የወቅቱን ሕገ መንግስት ለማሻሻል ሞክሯል።

ምንም እንኳ እኒህ ለውጦች ውጥረቱን ቢያረግቡም፣ በኋላ ላይ በኮሎኔል አለም ዘውድ የሚመራ የዘውዱ ተቆርቋሪ ቡድን የእንዳልካቸውን አስተዳደር ለመጥቀም በማሰብ ብዙ የአየር ኃይል መኮንኖችን ለእስር ዳረገ። በዚህ ሁኔታ የተበሳጨውና ተከፋፍሎ የነበረው የጦር ሠራዊቱ ክፍል፣ ኮ/ል አለም ዘውድ ከሚመራው ቡድን በማፈንገጥ በአንድ ልብ አመጽ ጀመረ። ሻለቃና ከሻለቃ በታች የሆኑት እነዚህ መኮንኖች በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የአገሪቱ ሰራዊት ሶስት ሶስት ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ በማድረግ፣እርስ በርሳቸው በመሰባሰብ፣ ደርግን መሰረቱ።

ኮ/ል አለም ዘውድ የዘውዱ ተቆርቋሪ እንደሆነ ከታመነበት በኋላ በኮ/ል አጥናፉ አባተ የሚመራ፣ በአብዛኛው ከሆለታ ጦር ማሰልጠኛ የተመረቀ ቡድንና ጥቂት የሐረር መኮንኖች ማሰልጠኛ ምሩቆች ሆነው አክራሪ አብዮተኛ ቡድን መስርተው ከአለም ዘውድ ቡድን ተገንጥለው ወጡ። ይህ ቡድን በኮሚቴ በመዋቀር በአገሪቱ ከሚገኙ 42 የጦር ክፍሎች ሦስት ሦስት ወኪሎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ ከሰኔ ’66 ጀምሮ መደበኛ ስብሰባ በማድረግ ደርግ እንዲቋቋም አደረገ።

በአነጋገር ጥንካሬ፣ ውሳኔ ለመወሰን ባለማመንታቱ ታዋቂነት ያተረፈው መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መፈክር ካስተዋወቀ በኋላ በጣም ተቀባይነትን በማግኘቱ የዚሁ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መፈክር ባስተዋወቀበት ንግግሩ ኮሚቴው ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ ለማዳን የቆመ ኃይል አድርጎ በማቅረብ ለተዘበራረቀው አብዮት አቅጣጫ ከመስጠቱም በተጨማሪ የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ የሚችል ሃይል ይሄው ኮሚቴ እንደሆነ በማሳየት ለኮሚቴው የሃገር ጠባቂነትን አላማ ለማሰጠት ችሎ ነበር።

መንግስቱ፣ ምንም እንኳ በወታደሩ ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ በመላው ሃገሪቱ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነትን ማግኘት እንደማይችል ስለተረዳ ለዚህ ተግባር እንዲረዳው ጄኔራል አማን አንዶምን የስርዓቱ መሪ እንዲሆን በመጋበዝ የጊዜያዊው አስተዳደር ደርግ መሪ እንዲሆን አደረገ። ቀጥሎም ለዓፄ ኃይለሥላሴ 5 ጥያቄዎችን በማቅረብ ንጉሱ አምስቱንም ስለፈቀዱ የደርግ ሃይል በቅጽበት እንዲያድግ አደረገ።

በመቀጠል፣ በሃይል የጎለበተው ደርግ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳልካቸው ከስልጣን እንዲነሱ አድርጎ ሚካኤል እምሩን ተካ። አማን አንዶም መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ እንዳልካቸውና የርሳቸው ደጋፊዎች እንዲታሰሩ ተደረገ። በዚህ መልኩ ቀስ ብሎ ይካሄድ የነበረው ለውጥ ፍጥነት ጨመረ። መንግስቱ፣ ንጉሱ ራሳቸውን በቀጥታ መጋፈጥ ስላልፈለገ ቀስ በቀስ የኃይላቻውን መዋቅር በማፈራረስ፣ የክብር ዘበኛን መሪ በማሳሰር፣ በኋላም የጆናታን ዲምብሊን የወሎ ረሃብ ቪዲዮ በቴሌቪዥን በማቅረብ ንጉሱ ተጠያቂ መሆናቸውን በማሳየት፣ ሙሉው ስራ ከተሰራ በኋላ ያለምንም ችግር ንጉሱን ከስልጣን ማስወገድ ቻለ።

የኮለኔሉ ሽሽት

በህዝባዊ አመጽ ከዙፋናቸው የወረዱት የአጼ ሀይለስላሴ አገዛዝ ከተገረሰሰ አንስቶ ኢትዮጵያን ለ17 አመታት እንደፈቀዱ ሲገዙና ሲነዱ የቆዩት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ሲያሳድዷቸው በነበሩ ተዋጊዎች ተገፍተው አበቃላቸው:: በሰሜን ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነዚህ ታጣቂ ሀይሎች ድል እየቀናቸው ወደ አዲስ አበባ መቃረባቸውን ተከትሎ ኮሎኔሉ ሸሽተው ከሀገር የወጡት የዛሬ 30 ዓመት ግንቦት 13 ቀን 1983 አ.ም ነበር::

እለቱ ማክሰኞ ነበር:: በስድስት ሰዓቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የዜና እወጃ፣ በሀገሪቱ የነበረውን ደም መፋሰስ ለማስቆም ሲባል ፕሬዚዳንት መንግስቱ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉን ተናገረ:: በማግስቱ ግን ለማንም ሳያሳውቁ ሸሸተው፣ መሄዳቸውን የመንግስት ምክር ቤት መግለጫ ሰጠ::

ሌፍተናንት ጀነራል ተስፋዬ ገ/ኪዳንም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሰየሙት ይህን ተከትሎ ነው:: ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ፣ በ1966 አ.ም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅ በአዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት እጃቸው ያስገባው ወታደራዊ ጁንታ (ደርግ) ሊቀመንበር ነበሩ::

ኮሎኔሉ የወቅቱ ገዥ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ /ኢሠፓ/ ዋና ፀሀፊ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በሚል በተደራረቡ ሹመቶች ራሳቸውን ሾመው ኖሩ:: ይሁንና አስተዳደራቸው ገና ከጅምሩ ግድያን መፍትሔ በማድረጉ ተቃዋሚያቸው እየበዛ ከመምጣትም ባሻገር፣ ተቃዋሚ ሀይሎች ጠመንጃ አንስተው ጫካ በመግባት ለአመታት ሲዋጉ ቆይተው ድል እየቀናቸው መጡ::

በ1983 ዓ.ም አጋማሽ ላይ፣ ተቃዋሚው የኢህአዴግ ሰራዊትም ወደ አዲስ አበባ በአሸናፊነት ገሰገሰ:: ተቃዋሚዎቻቸው እንደተጠጓቸው ያዩት ኮሎኔል መንግስቱ፣ “እኛ የምንሞተውም የምንኖረውም እዚሁ ሀገራችን ነው፤ አንድ ሰው እና አንድ ጥይት እስከሚቀር እንዋጋለን፤ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት” የሚሉት መፈክሮቻቸውን ጥለው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ኬንያ ሸሹ::

ወደ ኬንያ የሚሄዱበት አውሮፕላን እንዲዘጋጅላቸው ያዘዙት ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ ገብተው ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ የነበሩትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እጎበኛለሁ በሚል ሰበብ ነበር:: ከብላቴ ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በሚል አውሮፕላኗ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ:: ረፋድ ላይ በረራቸውን ጀመሩ፤ በአየር ላይ እንዳሉ አውሮፕላኑ ወደ ናይሮቢ እንዲበር አስገደዱት:: አብራሪው፣ አቅጣጫ ማሳያ ካርታ አለመያዙንና መብረር እንደማይችል አሳወቀ:: ኮሎኔል መንግስቱ ግን “በግድ ትሄዳታለህ” ብለው አስገድደው አቅጣጫ አስለወጡት::

በዚህ ድርጊታቸውም፣ የሀገር መሪ ሆነው፣ አውሮፕላን ለመጥለፍ፣ የመጀመሪያው መሪ ሆነዋል የሚሏቸው ወገኖች አሉ:: ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛው ፀሀፊ ተቀበሏቸው:: በዚያው የስደተኝነት ኑሯቸውን ወደሚገፉበት ዚምባብዌ ሀራሬ ከአምስት አጃቢዎቻቸው ጋር ሄዱ::

ኮሎኔል መንግስቱ፣ በስልጣን ዘመናቸው ሀገሪቱን እርስ በእርስ በሚያፋጅ ፖሊሲ፣ ለስልጣናቸው ቅድሚያ ሰጥተው፣ ሀገሪቱን የስቃይ እና የፍዳ መፈልፈያ አድርገዋታል፣፡ ታይቶ ከማይታወቅ ውርደትም ከቷት በሚል የሚከሷቸው አሉ:: አንዳንዶች ደግሞ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የመሬት አዋጅን የመሳሰሉ በማውጣት ለማስፈፀም ጥረት ያደረጉ ቆራጥ መሪ ይሏቸዋል::

ሁሉም ግን በስልጣን ጥማት የታወሩ እና በስልጣናቸው ከመጡባቸው ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ የማይታቀቡ አምባገነን መሆናቸውን ይናገሩላቸዋል:: በዘመነ መንግስታቸው፣ እርስ በርስ በተደረገ ፍጅት እና ጦርነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች ማለቃቸውም ይነገራል::

የዲሞክራሲ መብቶች የሚባሉ ነገሮች እንኳን በእውን በሕልም የማይታሰብበት፣ ሀገር ማለት መንግስቱ እና ፓርቲው ብቻ ሆነው እንዲታሰቡ የሚያደርግ አመራር የሚከተሉ ነበሩ ይሏቸዋል:: መጨረሻቸው ግን ይህን የሚገልጽ አልነበረም፤ የፎከሩበትን ሁሉ ሳይፈፅሙ፣ ደጋፊዎቻቸው የሰጧቸውን “ቆራጡ” የሚል ስያሜ ተግባራዊ ሳያደርጉ፣ ሁሉንም ጥለው ፈረጠጡ:: ኮሎኔል መንግስቱ አሁንም በስደት በሀራሬ ይኖራሉ::

ሌፍተናል ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን በ8 ቀናት የስልጣን ቆይታቸው፣ በአዲስ አበባ እልቂት እንዳይፈፀም፣ ሰራዊቱ ጠመንጃውን እንዲያስቀምጥ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ሰሩ የሚባል ስራ አልታየም:: ኮሎኔል መንግስቱ በሸሹ በ8ተኛው ቀን፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ::

ምንጭ-አዲስ ዘመን ክምችት ክፍል፣ሸገር ራዲዮና ሌሎች የታሪክ መፃህፍት


Exit mobile version