Site icon ETHIO12.COM

‹‹…አገር የሞተ እንደሁ በምን ይለቀሳል?››

( በገነት ዓለሙ )

አገራችን ውስጥ ዛሬም በዚህ ቀውጢ ጊዜ ከዋናው የአገር የፖለቲካ ጥያቄ ይልቅ በአንፃራዊነት እንክትካች በሆኑና በማያጣድፍ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዋናውን የአገር የፖለቲካ ጥያቄ መፈታት፣ በዘላቂነትና በዋስትና በሚፈልጉ የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች ላይ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ትግል ችግራችንን እያባባሰ ነው፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ሊወስደን እያካለበንና እያስፈራራን ነው፡፡ የተስማማንበትና የተማማልንበት ዋናው የአገር የፖለቲካ ጥያቄ ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የመተላለፍ የለውጥና የሽግግር አጀንዳ ነው፡፡

ከአምባገነንነት፣ ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር ደግሞ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ የመንግሥት አውታራትን መገንባት ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ ኢወገናዊ ተቋማት ኖረዋት አያውቁም፡፡ ለአንድ ወይም ለሌላ የፖለቲካ ቡድን ታማኝ ወይም ደባል አገልጋይ የሆነ ገለልተኛ ሆኖ ያልታነፀ፣ እንዲያውም ፖለቲካኛ ሆኖ የተቀረፀ የመንግሥት አውታር ላይ ሌላ አካል በምርጫ ሥልጣን ሊይዝ አይችልም፡፡ የዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት በመሰለ የፓርቲ ወይም የግንባር ውስጥ ምርጫ ዙሪያና ውጤት ውስጥ እንኳን ስለመፈንቅለ መንግሥት ሲወራ የሰማነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ለአንድ የፖለቲካ ቡድን ታማኝ በሆነ አውታረ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ በኃይልና በጉልበት ሥልጣን መያዝም ‹‹ዋስትና›› የሚኖረው ያንኑ አውታረ መንግሥት አበራይቶ መልሶ በራስ አምሳል መገንባት የተቻለ እንደሆነ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ሕገ መንግሥታችንን በጽሑፍ ሲሉ እንዲኖሩት፣ ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት መገናኘት እንዲችሉ መጀመርያ ይህንን ቀዳሚ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ መንግሥታዊ አውታራትን ከቡድን ታማኝነት ማላቀቅ አለብን፡፡ ከቡድን ታማኝነት የተላቀቁ የመንግሥት አውታራት መገንባት አለብን፡፡

ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት በንግግርና በውድድር የሚያስተናብር የዴሞክራሲ መደላደል ይዘጋጅ ማለት የየትኛውም አስተሳሰብ (እሳትና ጭድ የሆኑት ጭምር) ወገኖች ድጋፍ የግድ ማግኘት ያለበት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ትግልና ጉዞ ይህን የመሰለ ‹‹እሳትና ጭዶችን›› ጭምር ማስማማት ያለበት አንድ የጋራ አደራ ላይ የማገናኘት ከባድና ረዥም ጉዞ አለበት፡፡ የየትኛውም አስተሳሰብና ዓላማ ወገኖች ድጋፍ ከለውጡና ከሽግግር ጋር መሆን አለበት የሚለው ‹‹እንቆቅልሽ›› ፍቺም ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡

ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ መግባት ቀርቶ ይህን ጉዞ ራሱን መጀመር ቀላልና የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ በአስተሳሰብ፣ በማኅበራዊ ግንኙነትና በመንበረ መንግሥቱ አውታራት ላይ የደረሱ ብልሽቶችን ማደስ ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለና ካጎሰቋቆለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ከዚያም ያለፈ ችግር ጣጣና አደጋ አለበት፡፡ ለውጡና ሽግግሩ ውስጥ የተለያየ አመለካከትና ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ብቻ አይደሉም፡፡ ከእነሱ ጋር ሃያ ሰባት ዓመት የተሠራና የተቆጠረ ግፍና ግፈኛ አለ፡፡ የግፍ ባለዕዳውም፣ ተበዳይም አለ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አውታረ መንግሥቱን በአጠቃላይ፣ መከላከያውንና ደኅንነቱን በተለይ በዕዙ ሥር ተቆጣጥሮት የኖረው የገዥው ቡድን አናት ኋላ ላይ እንዳየነው ሠራዊት በቀጥታ የማንቀሳቀስ አቅም ባይኖረውም፣ 27 ዓመታት ሙሉ የተሠራው ብልሽትና ንቅዘት ግን የተባለውን አቅምና ሥፍራውን ሙሉ በሙሉ ውልቅልቁና ዝርክርኩ እንዲወጣ ገና አላደረገም ነበር፡፡ ጥቅምት 24 የደረሰብን ጥቃትና ከዚም በኋላ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ውስጥ የምናየው የተደጋገመ ‹‹ውርደት›› የዚህ ሁሉ ዕዳ ውጤት ነው፡፡ በዚህ ላይ ‹‹እልም ያለው ጫካ››፣ ‹‹እልም ያለው ዱር›› ውስጥ ተረባርበው የከተቱትን የሚመስሉ በርካታ ጉዳዮች አብረውብናል፣ አሲረውብናል፡፡ ወይም እንይዘው እንጨብጠው ያጣን አስመስለውብናል፡፡ ዝርዝሩን ሁሉም ሰው፣ ወዳጅም ጠላትም አንድ ሁለት እያለ ሲቆጥረው የምንሰማው ነው፡፡ ‹‹ትግራይ››፣ ‹‹ሱዳን››፣ ‹‹ህዳሴ››፣ ‹‹ምርጫ›› ብሎ ማነብነብ የተለመደ ከሆነ ወራት ቆጥረናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ያልተያያዙ፣ ድንገትና ሳይተዋወቁ ኢትዮጵያ ለውጥና ሽግግር ላይ በአጋጣሚ የተገናኙ አይደሉም፡፡ ይህንን እንደ አመጣጡና እንደ ክፋቱ በማስተናገድ ላይ እያለን የተለያዩ ሐሳቦችን፣ የተለያዩ አስተያየቶችን፣ ልዩ ልዩ ቀላልና የዘወትር ጥያቄዎችን የማስተናገድና የማስተባበር ባህርይና ልምድ የሌለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የዘንድሮ የረመዳን ፆም በየክልሉ የተለያዩ ትንንሽ ከተሞች ጭምር እንደ ቀልድ፣ ተራ ሁነትና ዜና ሆኖ ያለፈውን የመንገድ ላይ አፍጥር አዲስ አበባ ላይ ማስተናገድና ዓይቶ ማለፍ ውጪ ነፍስ፣ ግቢ ነፍስ ሆነበት፡፡ የፐብሊክ ስፔስ (Public Space) ሕጎችና ደንቦቻችን፣ ተራ ማዘጋጃ ቤት ዓይነት የከተማ አስተዳደር ተቋሞቻችን፣ አብረውን የኖሩት፣ አብረን የኖርንባቸው ግንኙነቶቻችን መደናገጥና ፍርኃት እስኪገባቸው ድረስ ዝርክርካችን ዝርጥርጣችን ወጣ፡፡

ለዚህ ሁሉ የሚሳልና የሚፀልይ ደግሞ ከውስጥም ከውጭም ከቦናል፡፡ እውነትን ቀናም፣ ገልመጥ ብሎም ማየት የተሳነው ‹‹ዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብ›› የሚባለው ሌላ ታሪካዊ ስህተት ካልሠራሁ እያለ አገር ቤት ውስጥ፣ ጎረቤት አገሮች ድረስ ዘልቆ ገብቶብናል፡፡ ይህንን ተራ ሊባል የሚችል የአንድ የዘወትር የሕዝብ አደባባይ አጠቃቀም/አገልግሎት ጥያቄ መነሻ አድርጎ አገርን ውጤቱ ከማይታወቅ አዳላጭ ድጥ ያተረፉት፣ የሕዝባችን በቱግታ ለመግለብለብ አለመቻኮል ብቻ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ምርቃትና ፀጋ ግን ሁልጊዜም ዋስትናችን ሊሆን የሚችለው ተቋማዊና ሥርዓታዊ ስናደርገው ነው፡፡ ለውጡና ሽግግሩ የጀመረውን ዴሞክራሲ የማደላደል ተግባርና አደራ የሁላችንም ግዳጅ ስናደርገው ነው፡፡

አደባባይ ወጥቶ በ‹‹ሰው›› ፊት ሊያዋርደን ጥቂት የቀረው የእኩልነት፣ የዜግነት፣ የአደባባይ፣ የሕዝብ አደባባይ፣ ወዘተ መብት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተካተቱና እዚያም ውስጥ መተማመኛ በተሰጣቸው ዝርዝር መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚሸፈኑ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚደነግጋቸው መብቶችና ነፃነቶች፣ ኃላፊነቶችም ጭምር በተግባር ኑሮ ውስጥ የሚዳሰሱና የሚጨበጡ፣ ሥልጣን ላይ ካለው የትኛውም ቡድን ቁርጠኝነትም ሆነ መሃላ ውጪ የሚኖሩ ለማድረግ የተጀመረውን ለውጥና ሽግግር ዳር ማድረስ አውታረ መንግሥቱን የዴሞክራሲ፣ የመብትና የነፃነት ተቋማትን ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ መብቶቻችንን ከእርጥባን ባለፈ፣ ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኗኗሪያ ማድረግ ያልቻልነው ይህ ጉድለት ስላለ ነው፡፡

የአደባባይ፣ የመንገድ ሕግና ሥርዓታችን ከተራና ማዘጋጃ ቤታዊ አደረጃጀት አኳያ እንኳን በጣም ኋላቀርና ‹‹ውስጡን ለቄስ›› የሚባሉ ናቸው፡፡ ስያሜዎች እንኳን ፖሊሲ ባለቤት የላቸውም፡፡ መኪና ውስጥ ሆነን ስንጓዝ የግድ የምናነባቸው የመንገድና የአደባባይ ስያሜዎች ስም የወጣላቸው ጊዜ የተሰጣቸው ስለመሆኑ በእርግጠኛነት የሚነግረን፣ ይህ የመንግሥት ቃል ነው የሚለን የለም፡፡ በዚህ ሥሌት ለምሳሌ ፒያሳ የሚባል አደባባይ በመንግሥት ይፋዊ የስያሜ መዝገብ ውስጥ የለም፡፡ የመንግሥት የስያሜ ባህረ መዝገብ (ይህም ካለ) የሚያውቀው ደጎል አደባባይ ብሎ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ዝርዝር ኢንቬንቶሪ ለማቅረብ ጥናትና ምርምር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡

ሌላ ‹‹ፖለቲካ›› እና መሰንበቻችን የተፈጠረው አደገኛና ለማንም የማይበጅ ‹‹ፉክክር››› ውስጥ የገባሁ አይምሰልብን እንጂ፣ መስቀል አደባባይ ወደ አብዮት አደባባይ፣ መልሶ ደግሞ ወደ መስቀል አደባባይ የተለወጠው አገር ይህ ነው የምትለው የስያሜ አሠራርና ሥርዓት ሳታዳብር ነው፡፡ እንኳንስ ለሕግ ያልተበገረው የከተማም፣ የመንገድም፣ የአደባባይም የስያሜ አሠራራችን ይቅርና ምንጊዜም ከሕግ በታች ሆኖ የኖረው የሕዝብ በዓላት አወሳሰናችን እንዴት አድርጎ የአገር ማፈሪያ እንደሆነ የመስከረም 2 እና የግንቦት 20 ነገር ሐውልትና ምሳሌ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በሕግ መስከረም 1 ቀን የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ የተቀላቀለችበት ቀን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖት አገር ናት፡፡ የሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች አገር ናት፡፡ ይህን እውነት ማስተናገድ የሚያስችል መሠረታዊና ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛም አላት፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ›› ናቸው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ የእምነት መብት ይህን ያህል ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው ነው፡፡ በእኩልነት መብት ላይ ብቻ የተተወ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት የመንግሥትንና የሃይማኖትን ለየብቻ ‹‹ተከባብሮ›› መኖር ይደነግጋል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖትን በክብር ተራርቃችሁ ኑሩ ብሎ የወሰነውና ይህንን መርህ ማቋቋም የጀመረው ግን የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አይደለም፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የተሰጠው በ1980 ዓ.ም. የሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጭምር ነው፡፡

ደርግም፣ ኢሕአዴግም ልክ በሌላ ዘርፉ እንደሆነው ሁሉ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ቢሉም፣ መንግሥት ከእምነቶች ገለልተኛ ሆኖ መታነፅ በጣም ሲበዛ በእጅጉ በጣም ይቀረዋል፡፡ የተቋም ግንባታ ትግላችን፣ የለውጡና የሽግግር ጊዜ ሥራችን አምባገነንነትና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀናበሩ አውታራትን ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ታምነው እንዲያገለግሉ አድርጎ እንደገና ማዋቀር ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 መሠረት እንዲገዛ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ገና ዛሬም ከእምነቶች ገለልተኛ ሆኖ አልታነፀም፡፡ ይህ የሽግግር ወቅት ለዘላቂ ጥቅማችን በዋናው መነሻ ሥራችን ላይ የምንረባረብበት እንጂ፣ በዕለት ተዕለት አጋጣሚዎችና ‹‹ድንጋጤዎች›› እየበረገግን ሽግግሩን የምናሰናክልበት፣ በሽግግሩ ዙሪያ የተሰባሰበውን ድጋፍ የምናስደነግጥበት ጊዜ መሆን አይገባውም፡፡

ዝርዝሩ ውስጥ ስንገባ ብዙ የሚገርሙ፣ የሚያስደነግጡና የሚፈታተኑ ምናልባትም የማናልፋቸው ጥያቄዎችን የሚያነሱና ‹‹ዴሞክራትነታችንም ሆነ››፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታችንን›› አጋልጠው የሚያሳጡና የተደበቀ ሕመማችንን በሰው ፊት አዋርደው የሚያወጡ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ክፍት በሆነ አዕምሮ፣ ገለልተኛ በሆነ ስሜት ቀርበን መመርመር ይኖርብናል፡፡  

ብዙዎቻችን (ታላላቅ የሃይማኖት ሰዎችንና ዓለም አቀፋዊ የሲቪል ሰርቫንቶችን ጨምሮ) በሆነ የፖለቲካ ዝንባሌ፣ የብሔር ወይም የሃይማኖት ወገንተኝነት ውስጥ የማርገድ ፈተና ገጥሞናል፡፡ ለእውነትና ለእውነታ የመታመን አቅማችን ዳገት ላይ ተፈታትኖናል፡፡ የመብት ተቆርቋሪነት በወገን ሲለካ ዓይተን አፍረናል፡፡ የአመለካከት አድልኦን ባሸነፈ አዕምሮ በደልን መከላከል፣ ማጋለጥና ተጋፍጦ መፋረድ ላይ አንድ ላይ መግጠምና መሠለፍ እንቢ ሲለን ዓይተናል፡፡ የሙያ ኃላፊነትና አደራ የትኛውንም ዓይነት ዝንባሌና አቋም በልጦ ሲወጣ ማየት ያልዘሩትን ማፈስ ሆኖብናል፡፡ የብሔር ሠፈርንና የፖለቲካ ዝንባሌን፣ የሃይማኖት ካምፕን የተሻገረ ሚዛናዊነትንና ለኃላፊነት መታመንን ፈልጎ ማጣት ችግር እስኪሆንብን ድረስ ባዝነናል፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀውስ ለመዳን የሁላችንም ማነጣጠሪያ አሁን ያለው የሕግ ማዕቀፍ መሆን አለበት፡፡

ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ፣ ሌሎች መለወጥ የምንፈልጋቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚገርምና በጭራሽ የሚያጣላና የሚያናጭ መሆን የለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱን መቀየር፣ አልፈልገውም ማለት አንድ ‹‹ፍላጎት›› ነው፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት የለባቸውም ሌላው ‹‹ጥያቄ›› ሊሆን ይችላል፡፡ የመሬት የግል ሀብት መሆን ወይም ሌላ አማራጭ ከንግግር/ከውይይት በላይ የሆነ አጀንዳ አይደለም፡፡ ባለው ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ‹‹ኢድ አደባባይ››ም፣ ‹‹መስቀል አደባባይ››ም ብሎ ነገር የለም፡፡ ወይም አለ ብሎ ሐሳብን መግለጽና መወያየት፣ በዚህም ሒደት ውስጥ የሥርዓቱን ብይን መቀበል አገር ማንቀጥቀጥ ያለበት ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ጋር ገና ከአምባገነንት ወደ ዴሞክራሲ በምናደርገው ሽግግርና ለውጥ መባቻ ውስጥ ብልጭ ያለው ነፃነት የግርግር መደገሻ እንዲሆን መፍቀድም፣ ዘላቂውን ጥቅም ከቅርብ ጊዜ ‹‹ድል›› ጋር ማምታታት ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቁ ድል ይህ ወይም ያኛው አማራጭ ማሸነፍ አይደለም፡፡ መጀመርያ ሁሉም አማራጮችን በነፃነት ማቅረብ የሚቻልበትን አማራጮችም ቀርበው በእርጋታ፣ በለዘበ ስሜት፣ በዝግታ ተገላብጠው፣ በደንብ ተመክሮባቸው በሕዝባዊ አወሳሰን ዕልባት የሚያገኙበት ሁኔታ ማደላደል የሁሉም (የተለያየ አማራጭ ያላቸው በአማራጮቻቸው የሚጣሉ ወገኖችም ጭምር) የጋራ መነሻ መሆን አለበት፡፡

ዞሮ ዞሮ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ለእምነቶች ሰላም እኩልነትና ነፃነት የመንግሥት ከሃይማኖት ገለልተኛ ሆኖ መደራጀቱ ታላቅ መፍትሔ ነው፣ መተኪያም የለውም፡፡ የአንድ አገር ሕዝብ ከሞላ ጎደል የአንድ ሃይማኖት (የክርስትና ወይም የእስላም) ተከታይ ቢሆን እንኳን በሃይማኖት ጥቅል አንድነት ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸው አይቀርም፣ አለም፡፡ በዚህ ጊዜ መንግሥት የሃይማኖት ወገንተኛ ነን ካለ ወይም ከሆነ ወደ አንዱ የልዩነት ወገን ተንሸራቶ ከማዘንበልና ከማድላት፣ አንዱን ስህተተኛ አድርጎ ከማፈንና ከሥር ከማድረግ አያመልጥም፡፡ ይህ እስኪጨበጠን ድረስ፣ ተጨብጦንም ሕጉ መሬትና ሥር ይዞ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ከሃይማኖት ጋር የተገመደ የበላይነት ትግል መንግሥትን መገልገያው አድርጎ ማዋሉ፣ የፖለቲካ ትግልም ከሃይማኖት ጋር እየተቧካ መንገድ መሳቱ ይቀጥላል፡፡

መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በአገር የበላይ ሕግ፣ አሁን ዛሬ በዚህ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከ1980 ጀምሮ የተደነገገ ሆኖ ኖሯል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ችግር ከየትኛውም እምነትና ሃይማኖት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የታነፀ መንግሥት አለመኖሩ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የማደላደል ሥራችን መትጋትና መረባረብ ያለበት አንዱ የትግል ግንባር ይኼኛው ነው፡፡ መንበረ መንግሥቱን ወይም የመንግሥት አውታራትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅና የማለያየት መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት አይደለም፡፡ የትኞቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት ወይም ሚና ሥር እንዳይወድቁ፣ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኝ መጠበቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህንን መርህ የቆነጠጠ፣ የእምነት እኩልነትን የሚደነግግ፣ የእምነት መብትን፣ ያለ ማመን መብትን ጭምር የሚያቋቁም፣ እምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገደብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና ዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ አሠራር በሕገ መንግሥት መደንገጉ ጥሩ መነሻና ከፍ ያለ ጥንካሬ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዳይኖር፣ መንግሥት ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ ሕገ መንግሥት የተመሠረተበት መደላድል ነው፡፡

በየትኛውም ዘርፍ የተደነገገ፣ ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የተሰጠው የእኩልነት መብቶችንም ሆኑ፣ የእምነት መብትና ነፃነት ከችሮታና ከመንግሥታዊ ሥልጣን በጎ ፈቃድ የዘለለ ህልውና አጥተው፣ ከሲታና ምስኪን መፃጉዕ ሆነው የኖሩት ግን ከሕግ የቀረ ነገር ኖሮ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አውታረ መንግሥት ገለልተኛ ሆኖ መዋቀር ስለሚቀረውና ስላልቻለ ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት የሁሉም መብትና ነፃነት ይሁን ብሎ የዚህም ዝርዝር ህልውና በየሕይወት ዘርፉ ሲፈጸም ለመመስከር ሁሉም የተለያየ ሃይማኖት ተከታይ፣ ያለ ማመን መብት ባለቤትም ጭምር አስቀድመው ይሟላላቸው ዘንድ የሚጠይቁትና እነሱም ሊተባበሩት፣ ሊጋደሉበት የሚገባ ዴሞክራሲን የማደላደል ተግባርና ግዴታ አለ፡፡

ይህንን ዋነኛ የአገር ግዴታና ግዳጅ ሳያሟሉ፣ ዋናውን ግንዱን እየዘነጉ በአንፃራዊነት ‹‹ጭራሮ››ውና ርጋፊው ላይ መዋደቅ በመላው የሕዝብና የአገር ህልውና ላይ የሚቃጣ፣ የገዛ ራሱን የማጥፋት ደመኛና ክፉ ዕርምጃ ነው፡፡ የአገራችን ሰው በሌላ ሁኔታ በሌላ ድባብና ዓውድ፣ ‹‹…አገር የሞተ እንደሁ በምን ይለቀሳል?›› የሚለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ የተወሰደ


Exit mobile version