ETHIO12.COM

ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንደሚሰሩ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገለጹ


ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንደሚሰሩ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ገልጸዋል፡፡

በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በውይይቱ ባስተላልፉት መልዕክት፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ወገኖች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እየወሰዱት ያለውን ያልተገባ ተጽእኖ ለመቋቋም በላቀ አንድነትና ቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

ተወያዮቹ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ትልቅ ተምሳሌት የሆነ የረጅም ዘመን አኩሪ ታሪክ ያላት እና መቼም ቢሆን የውጭ ጣልቃገብነትን ፈጽሞ የማትቀበል ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ መንግስት በኩል የሚደረገው ፍትሃዊ ያልሆነ ጫና በአስቸኳይ እንዲቆም እና የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማክበር በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያደረገው የሕግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ በውጭ የሚገኙ የሕወሃት ርዝራዦችና ተላላኪዎች ከሀገራችን ጠላቶች ጋር በማበር የአገሪቱን ስም የሚያጠለሹና የተሳሳቱ መረጃዎችን በሚዲያ በስፋት በማሰራጨት የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

“በአሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ትከከለኛው መረጃ ለሚመለከታቸዉ አካላትና ለሚዲያ እንዲደርስ በማድረግ ይህንን የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለማጋለጥ እንደምንሰራ ቁርጠኛነታችንን እናረጋግጣለን” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አለኝታ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ውስጥ እንዳይሳካ ለማደናቀፍና ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎች በእጅ አዙር የሚያደርሱትን ጫና እንደሚቀወሙ ተወያዮቹ ገልጸዋል፡፡

“በአሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች የምንገኝ ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያችን የሚገኙ የአሜሪካ መንግስት የስቴት እና የፌደራል ባለስልጣናትን፣ የኮንግረስ አባላትን እና ሴናተሮችን በማነጋገርና የጽሁፍ መልዕክቶችን በመላክ በሀገራችን ያለውን ትክክለኛ ገፅታ እንዲገነዘቡ እና በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመመራት የተሳሳተ አቋም እንዳያራምዱ ለማድረግ፣ እንዲሁም ሰሞኑን የአሜሪካ ሴኔት ያወጣውን ሪዞልሽን መልሶ እንዲያጤነው እና የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ጠንክረን እንደምንሰራ እናረጋግጣለን” ብለዋል ተወያዮቹ ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫቸው፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውን ወደ በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version