Site icon ETHIO12.COM

ዲፕሎማሲው ጥርስ እያወጣ ነው፤ ሲንሆፍ አዲስ አበባ ለውይይት ገቡ

በኢትዮጵያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብና የቪዛ እገዳ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደሌለው ያስታወቁት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ አዲስ አበባ መግባታቸው ታወቀ። ሴናተሩ አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ናቸው በማህበራዊ ገጻቸው ያስታወቁት። በዲፕሎማሲው በአሜሪካ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ሴናተሮች ድምጽ የሚሰማበትና የሚሰባሰብበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው።

‘‘የኢትዮጵያውያን ወዳጅ የሆኑትን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር፣ ጂም ኢንሆፍን ወደ ሁለተኛው ቤትዎ ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ’’ ሲሉ በፊስ ቡክ ገጻቸው አክብሮት ሰጥተዋቸዋል።

 “በቁርጥ ቀን ከእውነት ጋር አብረው ስለሆኑ እናመሰግናለን” በሚል የኢትዮጵያ አሜሪካን ሲቪክ ካውንስል የአድናቆትና የምስጋና ደብዳቤ የላከላቸው ጂም ኢንሆፍ፣ በተለየ የመጡበት ምክንያት ባይገለጽም፣ በወቅታዊ ጉዳዮች እንደሚመክሩ ታውቋል።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግን በተደጋጋሚ በተሰጠው ስም ” አሸባሪ ቡድን” እያሉ የጠሩት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ አስራ አራት ደቂቃ የፈጀ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። መዕቀቡ ይፋ በሆነ ማግስት ንግግር ያሰሙት ሴናተሩ ዲስኩራቸውን ሲጨርሱ፣ “የኢትዮጵያን ታሪክ በመረዳትና በማክበር” በማለት ያላቸውን ክብር ገለጹ። አስከተሉና ” ኢትዮጵያዊያን ወዳጆቼ ” ሲሉ ወንድማዊ ልሳን ተሞልተው ዳግም ክብር ሰጡ። ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ባደሙትና ባሴሩት ፊት ሆነው ” ወንድሜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ” አሉና “አብረንዎት ነን” የሚል ማረጋገጫ ሰጡ።

ይህን ባሉ ቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሲንሆፍ “አሸባሪው ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደስተኛ አልነበረም፤ ከመንግስትም ጋር አብሮ ለመስራት እንቢተኛ ሆነ፤ ተቃውሞውንም አገሪቷን በማወክ መግለጽ ጀምሮ ነበር፤ በዚህ የህወሓት ሽብር የተሞላበት አካሄድ የተነሳ የኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ድርጅት ብሎ ሰይሞታል፤ ይህንን አሸባሪ ድርጅት የአሜሪካ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት እኩል ማየት መጀመሩ ስህተት ነው፣ ተቀባይነት የለውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ጥረት እያደረጉ ነው” ብለው ነበር።

እሳቸው ይህን ከማለታቸው በፊት ኢትዮ 12 ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የአውሮፓ ዲፕሎማት ለጊዜው መዘርዘር የማይፈልጉት ነገር ግን እየተሰራ ያለ ስራ መኖሩን መግለጻቸው ይታወሳል። ከዛም በቀጣይ ኢትዮጵያዊያን ሲንሆፍን ባለቸው መድረጅና አውድ ሁሉ እንዲያመሰግኑ አሳስበው ነበር።

ሲንሆፍ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እሳቸውን መስል ሴናተሮችን በማሳመንና በማሰባብሰብ ትርጉም ያለው ስራ ይሰራል ብለው እንደሚያምኑ ዲፕሎማቱ በግርድፍ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። አንዳንድ አላማቸውን የሳቱ የተቃውሞ አግባቦች አገር ስለሚጎዳ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ፣ ሲያጋጥማቸውም በማውገዝ ኢትዮጵያን እንደማይወክል በመግለጽ መታገል እንደሚገባም አመልክተዋል።


Exit mobile version