Site icon ETHIO12.COM

” ከጎናችን ” ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ሳምንታዊ መግለጫ

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የክልሉን ብሎም የሀገራችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩን ለመወጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቋሙ የህዝብ የሰላምና ደህንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ የመዋቅርና የሰው ሀይል ስምሪት ማስተካከያዎችን ከማድረጉም በላይ ለአሰራር ያስቸግሩ የነበሩ ነባር ደንብና መመሪያዎችን አሻሽሏል እያሻሻለም ይገኛል፡፡

ከመሰረቱ የአማራ ህዝብን እንደ ጠላት ቆጥሮ መዋቅራዊ ጭቆናና ግፍ ሲያደርስ የነበረው አሸባሪው የህውሃት ቡድን ከአራት ኪሎ ከተባረረ ጀምሮ በግልፅና በስውር በክልላችንናበህዝባችን ሲያደርስ የነበረው ያልተቋረጠ ግፍ ወደ ለየለት ግልፅ ማጥቃት ሲሸጋገር ተቋሙ ለጊዜው የሚመጥን ዝግጅት በማድረግ ተገቢውን አመራር ሰጥቶ ጥቃቱን በሚገባ መክቷል፡፡አሸባሪው ቡድን ሀገርን ክዶና ደፍሮ በማዋረድ የተላለፈውን ቀይ መስመር ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት መክቶ የሀገር ባለውለታነቱን አስመስክሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራዎችን በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ በማድረግ በአንፃራነት የተረጋጋ ክልል ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡የለውጥ ስራ ሂደት በአንድ ጀንበር የሚቋጭ አይሆንም እና ገና ህዝባችን ያላረካንና የአገልግለት አሰጣጥ ጉድለቶች ያሉብን ስለሆነ ከህዝባችን ጋራ በመሆን ወደ ፊት የተሻለአገልግሎት አሰጣጣችን እንዲኖር የለውጥ ስራውችን እየሰራን እንገኛለን፡፡

ይሁን እንጂ ክልሉን ለመወጠር ከውስጥ እስከ ውጭ ተናበው የሚሰሩ ሀይሎች የሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥፋት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሰሜን ሽዋ አጣየእና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አካባቢ፤ በቅርቡም የቅማንት ፀንፈኛ ቡድን በተደራጀ መንገድ በጎንደር ከተማ ላይ አስቦት የነበረው ድርጊት የህዝባችን ሰላም ለማናጋት የክልሉን ሰላም የማደፍረስ ተልዕኮ አካል ነው ብለን እናምናለን፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ የፀጥታ ሀይላችን ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮና ተቀናጅቶ የባንዳዎችን እኩይ ድርጊት የቀለበሰ ሲሆን በቀጣይ የድርጊቱ ተሳታፊዎች እና የደረሰውን ጉዳት ጥልቅ ምርመራ በማድረግ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተቋማችን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለሰላም ወዳድ ህዝባችን ልናረጋገጥን እንወዳለን፡፡

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራር ያለፉና የቀጣይ ሁኔታዎችን በመገምገም የቀጣይ የቀሪ ወራት ቁልፍ ተግባራትን ለይቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የተቋሙ አሰራሮችን በመፈተሸና ችግሮችን ለይቶ ለመደገፍ በተለይም 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በክልላችን ያለምንን የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ሀይሉ ገለልተኝነት ያረጋገጥ ዕቅድና ስምሪት ተሰጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ለዚህም የመረጃና ደህንነት ስራዎችን በማጠናከር ከአጎራባች ክልሎች፣ ከፌዴራል የፀጥታ ተቋማት፣ ከብሄራዊ ደህንነት ጋር በትብብር እየተሰራ ሲሆን በአጠቃላይ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በቅድመ መከላከል ላይ የተመሰረተ ፖሊሳዊ ተግባራትን ለመከወን በምናደርገው ጥረት ህብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከጎናችን እንዲሰለፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

በጀግንነት መጠበቅ በሰባዊነት ማገልገል

አማራ ፖሊስ ኮሚሽን ግንቦት 25/2013 ዓ.ም


Exit mobile version