ETHIO12.COM

በባጃጅ ሆድ እቃ ዕቃ ተሸሽጎ ወደ ባህር ዳር ሊገባ የነበረ ሃያ ሺህ የሚጠጋ ተተኳሽ ጥያት ተያዘ

19 ሺህ 739 ተተኳሽ ጥይቶችን በባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህር ዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አለነ መሀሪ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ጥይቶቹን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ከገለጎ ከተማ ወደ ባህር ዳር ለማስገባት ሲሞክሩ ትላንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-43622 አማ በሆነ በባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህርዳር ለማስገባት ሲሞክሩ በሻውራ ጉምሩክ ሰራተኞችና በፌደራል ፖሊስ ትብብር በተደረገ የኬላ ፍተሻ መያዛቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተው ጉዳዩ እንዲጣራ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የማህበረሰቡንም ሆነ የሃገሪቱን ሰላም የሚጎዳ በመሆኑ ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ስራ አስኪያጁ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከባህር ዳር ዘግቧል።


Exit mobile version