ETHIO12.COM

 ኢትዮጵያ ዘመናዊ የባህርሃይል መገንባቷንና ጠላት ሁለቴ አንዲያስብ የሚያስገድድ ቁመና ያለው ጦር አንዳላት አስታወቀች

የባህር ሀይል ምክትል አዛዥ የሎጂስቲክ ሀላፊ ኮሞዶር ዋለጻ ዋቻ

አሁን ያለው የባህር ሀይሉ ዝግጁነት ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የኢፌድሪ የባህር ሀይል ምክትል አዛዥ የሎጂስቲክ ሀላፊ ኮሞዶር ዋለጻ ዋቻ አስታወቁ።ኢትዮጵያ ዘመናዊ የባህርሃይል መገንባቷንና ጠላት ሁለቴ አንዲያስብ የሚያስገድድ ቁመና ያለው ጦር አንዳላት አመልክተዋል፤

አሁን ያለው ሀገራዊ ወታደራዊ ቁመናችን አስተማማኝ፤ የትኛውም አይነት ጠላት በየትኛውም መንገድ ቢመጣ መቋቋም የሚያስችል እንደሆነ ገለጹ።

ኮሞዶር ዋለጻ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት ፣ በአሁኑ ወቅት ባህር ሀይልን እንደ አንድ ሀይል ለማደራጀት የሚያስችሉ ሥራዎች በሙሉ ተሰርተዋል ፤ ባህር ሀይል እንደ ባህር ሀይል አሁን ያለው ዝግጁነት ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ፣ ዛሬን ሳይሆን ነገ ከነገወዲያ በባህር ላይ ሊመጣ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል የሚችል ቁመና እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ነው።

 ባህር ሀይል ብቻውን አይደለም የሚሰራው አየር ሀይል፣ የምድር ሀይል እና ሌሎቹም ተናበው የሚሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ የትኛውም ዓይነት ጠላት ኢትዮጵያን ለመውረር ወይንም ደግሞ በሀገሪቱ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲያስብ ሁለት ሶስት ጊዜ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያስገድድ ቁመና ላይ እንደምንገኝም አመልክተዋል።

አየር ሀይል፣ ምድር ሀይል፣ ባህር ሀይልና ሌሎቹም የውጊያ አውዶች በመጣመርና ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ የአገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ተገንብቷል። የትኛውም አይነት ጠላት በየትኛውም መንገድ ቢመጣ ሊደፍረን አይችልም፤ ቁመናችን እጅግ አስተማማኝ ነው ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ጠላቶቻችን በቀጥታ ውጊያ እየገጠሙን አይደለም ያሉት ኮሞዶር ዋለጻ፣ ከዛ ይልቅ የእኛን ውስጣዊ ከፍተቶች በመጠቀም ላይ ናቸው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ሰራዊታችን በመደበኛነት ከሚያደርገው የአገርን ዳር ድንበር የማስጠበቅ ሥራ ውጪ እነሱ የሚፈጥሯቸውን ችግሮች በማርገብ ላይ እንዲጠመድ ሆኗል። ነገር ግን አሁን ያለው የሰራዊታችን ጥንካሬና አንድነት ከምንም በላይ ጠላትን ድባቅ መምታት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ዜጋም በውስጣችን ምንም ዓይነት የፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር ይችላል ነገር ግን በአገራችን ጉዳይ ላይ አንድ ነን፤ ሰራዊታችን ደግሞ ከአቀራረጹም ጨምሮ የተጠና በመሆኑ አሁን ላይ የማንም ፖለቲካዊ ድርጅት አስተሳሰብ የለውም፤ ከዛ ይልቅ የአገርን ሉአላዊነት ዳር ድንበር የማስጠበቅ ኃላፊነት ብቻ እንዳለው ተረድቶ በዛው መንገድ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

እንደ ኮሞዶር ዋለጻ ገለጻ ፣ አሁን ባለው ሁኔታ አየር ሃይል ምድር ሀይልን ብናይ አሉ የተባሉ ቴክኖሎጂ የተላበሱ፣ በአካል ብቃትና በስነ ምግባር የታነጹ ናቸው። የትኛውንም ጠላት ለመመከት የሚያስችል በቂ ሰራዊት አለን ። በባህር ሀይል ላይም የተመረጡ ለሙያው የሚገቡ ሰዎችን ከመመልመል ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ አገርም እየወሰዱ ያሉት ስልጠና እጅግ የተጠና ብሎም ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሁን ያለው ዝግጅት ባህር ሀይሉ በቀጣይ ትልቅ ሥራ የሚሰራ እንደሚሆን ያሳያል ያሉት ኮሞዶር ዋለጻ፣ አገራችንን እየተገዳደሩ የሚያስቸግሩ ጠላቶቻችንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተጣምሮ ግዳጅን ለመወጣት የሚችል በቂ ሞራልና ዝግጁነት እንዲሁም ብቃት ያለው ባህር ሀይል እንዳለም ጠቁመዋል።

እፀገነት አክሊሉ አዲስ ዘመን


Exit mobile version